(ዜና ፓርላማ)፤ ሰኔ 10፣ 2014 ዓ.ም.፤ አርባምንጭ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ታገሠ ጫፎ፤ ከጋሞ ዞን የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን፣ የአርባምንጭ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ ዛሬ ጎበኙ።

የተከበሩ አፈ-ጉባዔ በጉብኝታቸው ወቅት፤ በዕውቀት እና በሥነ-ምግባር የታነፁ ሀገር ተረካቢ ዜጎችን ለማፍራት በማቀድ የዞኑ አስተዳደር የአዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ በመጀመሩ አመስግነዋል።

ግንባታው በአጭር ጊዜ የተሻለ ደረጃ መድረሱን መታዘባቸውን የገለጹት አፈ-ጉባዔው፤ የትምህርት ቤቱ ግንባታ ተጠናቅቆ የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዲጀምር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው፤ የአርባምንጭ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ በጀመረ አጭር ጊዜ አፈጻጸሙ 40 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።

ግንባታው 26 የተለያዩ ሕንፃዎችን እንደሚያካትት የአስረዱት አቶ ብርሃኑ፤ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቅቆ፣ በ2015 የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር በትኩረት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

የአርባምንጭ አዳሪ ትምህርት ቤት ከ4 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነባ የሚገኝ ሲሆን፤ የ8ኛ ክፍል ክልል-አቀፍ ፈተና ወስደው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ 7 መቶ 20 የ9ኛ ክፍል ተማሪዎችን ተቀብሎ በ2015 የትምህርት ዘመን ሥራ እንደሚጀምር መረጃዎች ያመለክታሉ።

በጉብኝቱ የጋሞ ዞን ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችም መገኘታቸውን የጋሞ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ዘገባ ያመላክታል።