(ዜና ፓርላማ)፤ ጳጉሜ 2፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ታገሠ ጫፎ፤ በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ እና የባንግላዲሽ አምባሳደሮችን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡

ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ካደረጉት ከእነዚሁ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ጋር፤ የተከበሩ አፈ-ጉባዔ ሰሞኑን ከየሀገራቱ ጋር ስለሚኖረው የወዳጅነት እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች በተናጠል መክረዋል፡፡

ደቡብ ኮሪያ እና ኢትዮጵያ እጅግ የተለየ ታሪካዊ ቁርኝት እንዳላቸው ለደቡብ ኮሪያው አምባሳደር ያወሱት የተከበሩ አፈ-ጉባዔ፤ ይህ ለዘመናት ሥር ሰድዶ የኖረው ወዳጅነት በፓርላማ ለፓርላማ እና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶች ዳብሮ እንዲቀጥል ያላቸውን ምኞት ገልጸዋል፡፡

ደቡብ ኮሪያ በተለይ በሰው ኃይል ልማት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በምጣኔ-ሀብት ትስስር ከኢትዮጵያ ጋር የመሠረተቸው ግንኙነት አብነታዊ መሆኑንም አፈ-ጉባዔ ታገሠ አስረድተዋል፡፡

በተያያዘ ዜናም ባንግላዲሽ በማደግ ላይ ባለ ምጣኔ-ሀብታዊ ለውጥ ውስጥ ያለች ሀገር እንደ መሆኗ፤ ከሀገራችን ጋር የሚኖራት የፓርላማ ለፓርላማ እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲሁም ኢንቨስትመንት-ተኮር ግንኙነት አስፈላጊ እንደሆነ የተከበሩ አፈ-ጉባዔ አመልክተዋል፡፡

ሁለቱም አምባሳደሮች በየበኩላቸው የየሀገራቸውን ፍላጎት እና አቋም የገለጹ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያ ጋር በብዙ ዘርፎች በወዳጅነት እና በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ከኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

በ አሥራት አዲሱ

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት

በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament

በዩቲዩብ https://www.youtube.com/watch?v=cp_8F5TEeFE

በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews

በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr

በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ