(ዜና ፓርላማ)፤ ሰኔ 15፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ አቶ ታገሠ ጫፎ፤ በፌዴራል ኦዲተር ጄኔራል ቢሮ በኩል የሚቀርቡትን የፋይናንስ እና የክዋኔ ኦዲት ግኝቶችን መሠረት በማድረግ፣ ፓርላማው በተገቢው ደረጃ እንዲከታተል አሳሰቡ።

የተከበሩ አፈ-ጉባዔ ለ6ኛው ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 15ኛ መደበኛ ጉባዔ በሰጡት አቅጣጫ፤ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች እና አባላት በክትትል እና ቁጥጥር ሥራቸው ወቅት፣ ምክር ቤቱ ራሱ የአጸደቀው በጀት ለታቀደለት ዓላማ መዋሉን፤ ጠበቅ አድርገው መከታተል አለባቸው ብለዋል።

ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት የፌዴራል በጀት በአግባቡ ሥራ ላይ መዋሉን መከታተል እና የኦዲት ግኝቶችንም ለምክር ቤቱ የማቅረብ ስልጣን እንዳለው፤ አፈ-ጉባዔው አስታውሰዋል፡፡ የአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎችም የኦዲት ሪፖርት ሲቀርብ የመገኘት እና የመከታተል ግዴታ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

የኦዲት ሪፖርቱ ለሁሉም አስፈጻሚ አካላት ደርሶ ተገቢው ማስተካከያ እንደሚደረግ እና የማስያተካክሉ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ እንዲሁም አስተዳደራዊ ርምጃ እንዲወሰድ እንደሚደረግም አስገንዝበዋል፡፡

ምክር ቤቱ በውሎው በዋና ኦዲተር የቀረበውን የፌዴራል መንግስት መሥሪያ ቤቶችን የ2013 በጀት ዓመት ሒሳብ የፋይናንስ ሕጋዊነት እና የክዋኔ ኦዲት ዝርዝር ሪፖርት አዳምጧል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ ባቀረቡት ግብረ-መልስ፤ የፌዴራል ዋና ኦዲተር የመንግስት እና የሕዝብ ሀብት በትክክል ስራ ላይ እንዲውል ለማድረግ ይረዳው ዘንድ፣ በተቋማዊ የሰው ኃይል እና መረጃ አደረጃጀት ረገድ ያከናወናቸውን ተግባራት በጠንካራ አፈጻጸም ወስደዋል፡፡

በሌላ በኩልም በቀጣይ የኦዲት ግኝት የቀረበባቸው ተቋማት የወሰዱትን የማስተካከያ ርምጃ እንዲያሳውቁ፣ ወቅቱን ጠብቀው ሒሳብ የማይዘጉ መሥሪያ ቤቶች ሒሳባቸውን በወቅቱ እንዲዘጉ፣ የሥራ ኃላፊዎች በኦዲት መግቢያ እና መዝጊያ ስብሰባዎች እንዲገኙ እና ግብዓት እንዲሰጡ፣ ኦዲት ተደራጊ መሥሪያ ቤቶች ለኦዲተሮች ምቹ ቢሮ እንዲያዘጋጁ፣ ሁሉም መሥሪያ ቤቶች የኦዲት ሪፖርታቸውን ለሠራተኞች እንዲያሳውቁ እና የዕቅዳቸው አካል እንዲያደርጉ ቋሚ ኮሚቴያቸውን ወክለው አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

አያይዘውም፤ ተቆጣጣሪ አካላት የዋና ኦዲተርን የኦዲት ሪፖርት በግብዓትነት መጠቀም፣ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትም ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር፣ በአንድ የምርጫ ዘመን ተከታታይ የኦዲት ግኝት ሪፖርት ላይ ተቀባይነት የሚያሳጣ የሚል አስተያየት የቀረበባቸውን መሥሪያ ቤቶች የመሩ የሥራ ኃላፊዎች ለመንግስት የሥራ ኃላፊነት የማያበቃ በሚል መያዝ እንዳለባቸውም በግብረ-መልሳቸው አመላክተዋል፡፡

የኦዲት ሪፖርት ሲቀርብ ደግሞ፤ ሁሉም የምክር ቤቱ አባላት እና የባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች መገኘት እና መከታተል አለባቸው ብለዋል፡፡

በ ኃይለሚካኤል አረጋኸኝ