(ዜና ፓርላማ)፤ ሐምሌ 07፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ የምጣኔ-ሀብት ዘርፏን ለማስፋት፤ ከደቡብ ኮሪያ ሪፐብሊክ ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆኗ፣ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተገለጸ፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) ይህንን የገለጹት፤ የደቡብ ኮሪያን አምባሳደር ካንግ ሴኦክሄን በዛሬው ዕለት በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ነው ፡፡

የተከበሩ ዲማ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ የምጣኔ-ሀብቷን ዓይነት እና መጠን ለማስፋት ባላት የዘወትር ዓላማ መንስዔ፤ በንግድ፣ በግብርና እና በኢንቨስትመንት ዘርፎች ከደቡብ ኮሪያ ጋር ተባብራ ትሠራለች ብለዋል፡፡

በተለይም በንግዱ ዘርፍ ያለውን የሁለቱን ሀገራት ትስስር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለማስፋት፤ ኢትዮጵያ ወደ ደቡብ ኮሪያ በምትልካቸው ምርቶች ላይ ደቡብ ኮሪያ የታሪፍ ማሻሻያ እንድታደርግም፣ ሰብሳቢው ጠይቀዋል ፡፡

ኢትዮጵያ በብረታ-ብረት እና በተለያዩ የማዕድናት ክምችት ዕምቅ ሀብት እንዳላት ያብራሩት የተከበሩ ዲማ (ዶ/ር)፤ የደቡብ ኮሪያ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በዘርፉ እንዲሰማሩ በአምባሳደሩ በኩል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የደቡብ ኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ካንግ ሴኦክሄን በበኩላቸው፤ ሀገራቸው የምጣኔ-ሀብት ተደራሽነቷን ለማስፋት በንግድ፣ በግብርና እና በኢንቨስትመንት ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር ተባብራ እንደምትሠራ አስታውቀዋል፡፡

አምባሳደሩ አክለውም፤ የምጣኔ-ሀብት ዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ እንዳይንቀሳቀስ ዓለም-አቀፍ ፈተና እየሆነ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ፤ ደቡብ ኮሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ተባብራ ትከላከላለች ብለዋል፡፡

አምባሳደሩ አያይዘውም፤ በኢትዮጵያ ያለውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት ደቡብ ኮሪያ ፍላጎት እንዳላት ገልጸው፣ የችግሩ ሰለባ ለሆኑ ዜጎች ሰብዓዊ ርዳታ ለማቅረብ የደቡብ ኮሪያ መንግስት መወሰኑንም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡- በ ስሜነው ሲፋረድ

ቀን፡- ሐምሌ 07፣ 2014 ዓ.ም