(ዜና ፓርላማ)፣ ነሐሴ 4፣ 2014 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ እና ቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በማጠናከር በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የበለጠ በትብብር እንደሚሰሩ መክረዋል፡፡

ይህ የተገለጸው በዛሬው ዕለት የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ወይዘሮ ሎሚ በዶ በኢትዮጵያ የቻይና ተጠባባቂ አምባሳደር ሼን ኪንሚን በምክር ቤቱ ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ነው፡፡

ኢትዮጵያ እና ቻይና ዘመናትን ያስቆጠረ ረጅም ታሪክ እና ዘርፈ-ባዙ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ ይህን መልካም ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በትብብር እየሰሩ እንደሆነ ምክትል አፈ-ጉባዔዋ ገልጸዋል፡፡

የሁለቱ ሀገር ሕዝቦች በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚ በሚሆኑባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተባብረው እንደሚሰሩ ወይዘሮ ሎሚ በዶ አስገንዝበዋል፡፡

የሁለቱን ሀገሮች የቆየ ወዳጅነት በማጎልበት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡበት እና በተለይም በፓርላማ አቅም ግንባታ ስራዎች ዙሪያ በትብብር እንደሚሰሩ በውይይቱ ተመላክቷል፡፡

በምክር ቤቱ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ክቡር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እና ቻይና ረጅም ታሪክ ያላቸው እና ሁለቱም በቅኝ ያልተገዙ፣ነጻነታቸውን ለዘመናት አስከብረው የኖሩ ሕዝቦች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የቻይና ሕዝብ ጠንካራ የስራ ባህል ያለው በመሆኑ አደንቃለሁ ያሉት ክቡር አቶ ተስፋዬ፤ በኢትዮጵያ የቻይና ኢንቨስትመንት መስፋፋትን ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የሚደረገው ትብብር የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቻይና ተጠባባቂ አምባሳደር ሼን ኪንሚን በበኩላቸው ኢትዮጵያ እና ቻይና የቆየ መልካም ግንኙነት እንዳላቸው እና አሁንም በተለያዩ ዘርፎች ተባብረው እየሰሩ እንደሆነ ገልጸው በቻይና በኩልም በፓርላማ አቅም ግንባታ ዙሪያ በትብብር እንደሚሰሩ አመላክተዋል፡፡

ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር በኢንቨስትመንት፣ በትምህርትም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ያለውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ተስፋሁን ዋልተንጉስ

ቀን፡- ነሐሴ 4፣ 2014 ዓ.ም