(ዜና ፓርላማ)፣ ነሐሴ 23፣ 2014 ዓ.ም፤ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ ፓርላሜንታዊ ግንኙነታቸውን የበለጠ በሚያጠናክሩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

የሁለቱን ሀገሮች የቆየ የወዳጅነት ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ የመከሩት፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮ ቋሚ ኮሚቴ እና የደቡብ ኮሪያ የምክር ቤት አባላት ናቸው፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ፈቲሂ ማህዲ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ የረጅም ጊዜ የወዳጅነት ግንኙነት እንዳላቸው በመግለጽ ለአብነትም የኢትዮጵያ ወታደሮች በኮሪያ ሰላም ለማስከበር የከፈሉትን የህይወት መስዋእትነት አስታውሰዋል፡፡

ደቡብ ኮሪያ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት የምታደርገው ጥረት የሚደነቅ እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ፈቲሂ፤ በተለይም በኦሮሚያ ክልል ዱከም ከተማ የሚገኘው የብረታብረት ኢንዱስትሪ አንዱ ማሳያ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ የደቡብ ኮሪያ ባለሀብቶችም በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ እንዳለም አያይዘው ገልጸዋል፡፡

የተከበሩ ፈቲሂ ማህዲ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ለደቡብ ኮሪያ የምክር ቤት አባላት በገለጹበት ወቅት፤ መንግሥት በTPLF የተከፈተበትን ጥቃት በመመከት ከህግ ማስከበር ሥራው ጎን ለጎን ለትግራይ ሕዝብ የሰብአዊ እርዳታ እያደረገ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

TPLF ጦርነቱን በማራዘም አሁንም በአማራ እና በአፋር ክልሎች ጦርነት ከፍቶ ጥፋቶችን እየፈጸመ እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ፈቲሂ፤ በመንግስት በኩል ችግሩን በሰላማዊ ድርድር ለመፍታት ከመቸውም ጊዜ በላይ ዝግጁ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ መንግስት ተገዶ የገባበት ጦርነት እንደሆነም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በሀገሪቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ትልቅ ተስፋ የተጣለበት እንደሆነ ያስረዱት ዶክተር ፈቲሂ፤ የሰላም ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት እንዲያልቅ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ በማስረዳት ረገድ የደቡብ ኮሪያ መንግስትም ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮ ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ቶፊቅ አብዱላሂ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን የደቡብ ኮሪያ መንግስት ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት ገልጸው፤ በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ እና ሌሎችም የመሰረተ ልማት ችግሮች ስላሉ የደቡብ ኮሪያ መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

የደቡብ ኮሪያ ምክር ቤት አባል የተከበሩ ኪም ታኢሆ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ወታደሮች በኮሪያ ዘምተው ህግ ባያስከብሩ ኖሮ የአሁኗ ደቡብ ኮሪያ አትኖርም ነበር በማለት ገልጸው፤ አሁንም የሁለቱን ሀገሮች መልካም ግንኙነት ለማጠናከር በሁሉም ዘርፍ እንሰራለን ብለዋል፡፡

የተከበሩ ኪም ታኢሆ በዚህ ዙር የደቡብ ኮሪያ ምክር ቤት አባላት ወደ ኢትዮጵያ የመጡበት ዋናው አላማ የሚላከው የሰብአዊ እርዳታ በትክክል ለተቸገሩ የማህበረሰብ ክፍሎች መድረሱን ለማረጋገጥ እንደሆነ እና በተጨማሪነት ምን እንደሚያስፈልግ ለማወቅ ነው ብለዋል፡፡

አያይዘውም ኢትዮጵያ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት እንዳላት እና ይህንን ሀብት ጥቅም ላይ እንድታውል በሚደረገው እንቅስቃሴ ደቡብ ኮሪያ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ማድረግ እንደምትችልም ነው ያስታወቁት፡፡

የደቡብ ኮሪያ ምክር ቤት አባል የተከበሩ ኪም ሱንግናም በበኩላቸው የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር በቱሪዝም እና በግብርና ዘርፎች ትከረት ሰጥተን እንሰራለን ብለዋል፡፡

ደቡብ ከሪያ የኢትዮጵያን ውለታ ለመክፈል ከውይይት ባለፈ በተግባር የሚረጋገጥ ድጋፍ እንደምታደርግም የምክር ቤት አባላቱ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና የኢትዮጵያ እና የደቡብ ኮሪያ የፓርላማ የወዳጅነት ቡድን የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት ለማጠናከር በተለያዩ ዘርፎች ተወያይተዋል፡፡

የኢትዮጵያ እና የደቡብ ኮሪያ የፓርላማ የወዳጅነት ቡድን ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ጫላ ለሚ የሁለቱ ሀገሮች ህዝቦች በደም የተሳሰሩ መሆናቸውን ገልጸው ይህ መልካም ግንኙነት በጤና፣ በትምህርት እና በሌሎች ዘርፎችም መጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ ባለችበት በዚህ ፈታኝ ወቅት የሕዝቡን ችግር በተግባር ለማየት መምጣታችሁ የሚደገፍ ነው ያሉት ደግሞ የፓርላማ የወዳጅነት ቡድን ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ኪሚያ ጁንዲ ናቸው፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት

በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament

በዩቲዩብ https://www.youtube.com/watch?v=cp_8F5TEeFE

በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews

በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr

በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ