(ዜና ፓርላማ)፤ ሐምሌ 9፣ 2014 ዓ.ም.፤ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ ከፊንላንድ አምባሳደር ጋር በሁለቱ ሀገራት የፓርላማ ግንኙነት ዙሪያ ሐሳብ ተለዋወጠ።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ከፊንላንድ አምባሳደር ከክብርት አውቲ ሆሎፔይነን ጋር ሰሞኑን በነበራቸው ቆይታ፤ የሁለቱን ሀገራት የፓርላማ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ሐሳብ ተለዋውጠዋል።

የተከበሩ ሰብሳቢ ለፊንላንድ ፓርላማ ልዩ ተወካይ እና ለክብርት አምባሳደሯ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ውስጥ ስኬታማ ተግባራትን ማከናወን ብትችልም፤ በሂደቱ ደግሞ የተለያዩ ፈተናዎች ነበሩ ብለዋል።

በተለይ ከሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት የሰላም አማራጭን ተከትሎ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በዚህ ሂደት ኢትዮጵያ የራሷን ችግር በራሷ ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት፤ ፊንላንድ እንድትደግፍም ጠይቀዋል።

የፊንላንድ ፓርላማ የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ልዩ ተወካይ ሱልዳን ሰዒድ አሕመድ በበኩላቸው፤ ሀገራቸው የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በሰላም አማራጭ ለመፍታት የጀመረውን እንቅስቃሴ እንደምትደግፍ ገልጸዋል።

በዚህ ረገድም በኢትዮጵያ ሰላምን ማምጣት ዓላማ ያደረገውን የሁሉን-አቀፍ ብሔራዊ ምክክር እንቅስቃሴ ፊንላንድ ትደግፋለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ በቀጠናው መሪነቷን ለማስጠበቅ የራሷን ሰላም መጠበቅ እንደሚኖርባትም አመልክተዋል።

የሰብዓዊ ድጋፍ በየብስ እና በአየር ወደ ትግራይ ክልል ማጓጓዝ በድጋሚ መጀመሩን ፊንላንድ እንደምታደንቅ ገልጸዋል። አክለውም፤ የኢትዮጵያን እና የፊንላንድን የፓርላማ ለፓርላማ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

የፊንላንድ ፓርላማ ሐምሌ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. የ29 ዓመቱን ትውልደ-ሶማሊያዊ ሱልዳን ሰዒድ አሕመድን፤ በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ዘንድ ሰላምን የማምጣት ሂደት እንዲደግፉ በማለም ልዩ ተወካይ አድርጎ መሾሙ ይታወሳል።

የልዩ ተወካዩ መሾም፤ ፊንላንድ በቀጠናው ያሉ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ እና ከምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ፣ የሀገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በወቅቱ ገልጾ እንደነበር የሚታወስ ነው።

በ ስሜነው ሲፋረድ