(ዜና ፓርላማ)፤ ሰኔ 10፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የ2014 በጀት ዓመት የአሥር ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፤ ዘንድሮ "ኢትዮጵያ ታምርት!" በተሰኘ ንቅናቄ ውጤት ማምጣቱን ገለጸ፡፡

የኢፌዴሪ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በሪፖርታቸው፤ ንቅናቄው ከተጀመረ ወዲህ በተለያዩ ምክኒያቶች ሥራ አቁመው የነበሩ 1 መቶ 18 ኢንዱስትሪዎች ማምረት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ከዚህም ባሻገር፤ የ"ኢትዮጵያ ታምርት!" ንቅናቄ የዘርፉ ወሳኝ ጠቀሜታዎች በዜጎች ዘንድ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረጉን እና ብዙ ግብዓቶችን የአስገኘ እንደሆነም ክቡር ሚኒስትሩ አስታውሰዋል።

ከአምራች ኢንዱሰትሪው ዘርፍ በበጀት ዓመቱ አሥር ወራት ውሰጥ 4 መቶ 98 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ፤ 4 መቶ 18 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱንም ገልጸዋል፡፡

የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካትን በተመለከተም፤ የዕቅዱን 85 በመቶ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል፡፡ የነባር ኢንዱስትሪዎችን የማምረት ዓቅም ማሻሻልን በሚመለከት 60 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ፤ 49 ነጥብ 2 በመቶ ማድረስ መቻሉን እና የማምረት ዓቅማቸውን እንዳይጠቀሙ ያደረጉ ማነቆዎችን በቀጣይ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ለመፍታት መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል፡፡

የቅድሚያ ትኩረት የተሰጣቸው ዘርፎች የግብዓት አቅርቦት እንዲያገኙ በሀገር ውስጥ ከግብርና እና ከማዕድን ዘርፍ ጋር በመቀናጀት እየተሠራ መሆኑን እና ከውጭ ለሚገቡት ደግሞ የውጭ ምንዛሬ እንዲያገኙ ድጋፍ መደረጉን አብራርተዋል።

በበጀት አመቱ 79 ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ ታቅዶ በባለፉት አሥር ወራት 66ቱ ማምረት መጀመራቸውን እና 2 ሺህ 907 አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች መቋቋማቸውን እንዲሁም ለ158 ሺህ 724 ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።

ክቡር ሚኒስትሩ ከምክር ቤቱ ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶችም ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አማረች በካሎ (ዶ/ር)፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ነባር ችግሮችን ተቋቁሞ ካከናወናቸው ተግባራት ውስጥ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ያደረገው ጥረት ጥሩ ስለሆነ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል። የተጀመረውን ንቅናቄ፣ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የማነቃቂያ ሥራዎችን፣ ከቴክኖሎጂ አኳያ የተከናወኑ ሥራዎችን እንዲሁም ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በጥንካሬ አንስተዋል።

በሌላ በኩልም የኢንዱስትሪ ዘርፉ እንደ ሀገር ተስፋ የተጣለበት እና ትልቅ ኃላፊነት የተሰጠው በመሆኑ፤ ያሉበት ችግሮች ተቀርፈው በዓለም ተወዳዳሪ ለመሆን እና የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ ችግር ፈቺ የሆነ አሰራር እና ግልጽ ስትራቴጂ አዘጋጅቶ ሀገራዊ ኢኮኖሚው ላይ ለውጥ የሚያመጣ ሥራ መሥራት እንዳለበት፤ የቋሚ ኮሚቴያቸው ምክረ-ሐሳብ መሆኑን አመላክተዋል። ፍትሐዊ ሀገራዊ የኢንዱስትሪ ሥርጭት እና ተጠቃሚነት እንዲኖርም መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በ ፋንታዬ ጌታቸው