(ዜና ፓርላማ)፤ ሰኔ 15፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የፌዴራል ኦዲተር ጄኔራል ቢሮ፤ ለኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች 6ኛው ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 15ኛው መደበኛ ጉባዔ ባቀረበው ሪፖርት፤ በ2013 በጀት ዓመት ኦዲት የተገኘባቸውን መሥሪያ ቤቶች ይፋ አደረገ።

ዋና ኦዲተር ክብርት ወይዘሮ መሠረት ባቀረቡት በዚሁ ሪፖርት፤ በተመረጡ የፌዴራል መንግስት መሥሪያ ቤቶች ኦዲት መከናወኑን ገልጸዋል።

በዚህም ጋምቤላ እና ደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲዎች በድምሩ 1,513,651.45 ብር የጥሬ ገንዘብ ጉድለት እንደተገኘባቸው፤ ሐዋሳ፣ ሚዛን ቴፒ እና ቀብሪደሃር ዩኒቨርስቲዎች በድምሩ 1‚001,318.97 ብር በክፍያ መመሪያ ከተወሰነው የገንዘብ መጠን በላይ ተከፍሎ መገኘቱን ዋና ኦዲተሯ ተናግረዋል፡፡

የውዝፍ ተሰብሳቢ ሒሳብን በተመለከተም የሰነድ ሒሳብ በወቅቱ ለማወራረድ ሲጣራ፤ በ133 መሥሪያ ቤቶች እና በ26 ቅ/ጽ/ቤቶች 13,100,235,836.20 ብር እና በ4 መ/ቤቶች ከሥራ ተቋራጮች የሚፈለግ ያልተሰበሰበ 10,183,865.34 ብር በደንቡ መሠረት እንዳልተወራረደ፣ በተጨማሪም በ6 መ/ቤቶች እና በ7 ቅ/ጽ/ቤቶች ብር 106,841,610.27 ማስረጃ ባለማቅረቡ ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ ያልተቻለ ተሰብሳቢ ሒሳብ መኖሩም በኦዲት ሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ገቢ ካልሰበሰቡ መ/ቤቶች መካከል በጉምሩክ ኮሚሽን የቃሊቲ እና የድሬዳዋ ቅ/ጽ/ቤቶች በድምሩ 260‚995‚040.86 ብር፣ በገቢዎች ሚኒስቴር የመካከለኛ ግብር ከፋዮች የባሕር ዳር ገቢዎች ቅ/ጽ/ቤት፣ ምዕራብ አዲስ አበባ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅ/ጽ/ቤት እና የቅዱስ ጴጥሮስ ቲቢ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በድምሩ 85‚693‚695.95 ብር እንደሆነ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

ማስረጃ ባለመሟላት ምክኒያት የገቢውን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ስላልተቻለ የተሰበሰበውን ገቢ ሒሳብ ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ፤ በ7 መ/ቤቶች ከተለያዩ ገቢዎች የተሰበሰበው ገቢ 154,406,678.78 አስፈላጊ የሆኑ ማስረጃዎች ባለመሟላታቸው የገቢውን ሒሳብ ትክክለኛነት ማረጋገጥ አለመቻሉን ዋና ኦዲተሯ አስረድተዋል፡፡

ከላይ ከተዘረዘሩት አብነቶች በተጨማሪ፤ ክብርት ዋና ኦዲተር የሌሎች በርካታ መሥሪያ ቤቶችን የኦዲት ግኝት በሪፖርታቸው አካትተው አቅርበዋል። ፓርላማውም ቀጣይ አቅጣጫዎችን በተከበሩ አፈ-ጉባዔ ታገሠ ጫፎ እና ከሪፖርቱ ጋር ቀጥተኛ የሥራ ግንኙነት ባለው የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በተከበሩ ክርስቲያን ታደለ አማካይነት አመላክቷል።

በ መስፍን አለሰው