(ዜና ፓርላማ)፤ ሰኔ 19፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ለመደንገግ በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 4/2013 ላይ፣ ከባለድርሻ አካላት የተሰጡትን አስተያየቶች በግብዓትነት መውሰዱን ገለጸ።

ሰሞኑን በተካሄደው በአስረጂ እና ባለድርሻ አካላት መድረክ፤ የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ኢሳ ቦሩ፣ ረቂቅ አዋጁ አዋጅ ሆኖ ከመውጣቱ በፊት ባለድርሻ አካላት በአካል ተገኝተው የሰጡት ሐሳብ እና አስተያየት ሁሉ ዋጋ እንዳለው አስረድተዋል።

በረቂቅ አዋጁ የተመላከቱት ዝርዝር የሕግ ድንጋጌዎች ዝርዝር አፈጻጸሞች እንደሚያሻቸው በተጠቆመበት በዚህ ይፋዊ የሕዝብ የውይይት መድረክ፤ ሌሎችም ጠቀሜታ እንዳላቸው የታመነባቸው አስተያየቶች ተሰንዝረዋል። እናም፤ ቋሚ ኮሚቴው እንደየተገቢነታቸው እንደሚጠቀማቸው ከመድረኩ መሪዎች ተመላክቷል።

በመድረኩ በአስረጅነት የተገኙት የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሚኒስትር ዴኤታዎች ክቡር ዓለምአንተ አግደው እና ክቡር ውብሸት ሺፌራው (ዶ/ር) ናቸው። እነርሱም በተመሳሳይ፤ የቋሚ ኮሚቴውን ምክትል ስብሳቢ መደምደሚያ ተጋርተዋል።

ከሁለቱ አካላት በተጨማሪ፤ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የሕግ ክፍል እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም በውይይቱ የነቃ ተሳትፎ ሲያደርጉ መዋላቸውን መረዳት ተችሏል።

በ አሥራት አዲሱ