(ዜና ፓርላማ)፤ ሰኔ 20፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ሕግን እና መመሪያን ተከትሎ እንዲሠራ አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ይህንን ያሳሰበው፤ በዩኒቨርሲቲው የ2012 በጀት ዓመት የኦዲት ሪፖርት ላይ፣ በዛሬው ዕለት ይፋዊ የሕዝብ ውይይት ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡

በውይይቱም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ክርስቲያን ታደለ፤ ዩኒቨርሲቲው የኦዲት ግኝቱን በመልካም ተመልክቶ ለማረም እና ለማሻሻል ዝግጁ መሆኑ ጥሩ መሆኑን ተናግረው፤ ግኝቶቹን ለማሻሻል የተደረጉ ሙከራዎችም እንደዚሁ ጥሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የቀለብ ወጪን ሳይጨምር ከሦስት መቶ ሠላሳ ዘጠኝ ሚሊየን በላይ ያልተረጋገጠ ሒሳብ መኖሩን ገልጸው፤ ይህንንም ለማስተካከል ተቋሙ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት አመላክተዋል፡፡

በተደጋጋሚ የሚስተዋለውን የመመሪያ ጥሰት በተመለከተ፤ እያንዳንዱ ሰው ለሌላው ሠራተኛ ምሳሌ በሚሆን መልኩ አክብሮ መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ የመመሪያ ጥሰቱ ከባለሙያ ብቃት ማነስ ነው የሚለውን ምክኒያት ኮሚቴው እንደማይቀበለው እና ሲጀመር ዩኒቨርሲቲው አወዳድሮ ብቃት ያላቸውን ሠራተኞች መቅጠር እንደሚኖርበትም ጠቁመዋል፡፡

ከንብረት ጋር ተያይዞ ላለው ጉዳይ፤ ሕግ እና መመሪያን ሳይጥስ የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅሞ ንብረቶቹ ሳይበላሹ ጥቅም ላይ መዋል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ የተከበሩ ሰብሳቢ የሚከተሉትን አቅጣጫዎችም ለአሶሳ ዩኒቨርሲቲ አስቀምጠዋል፡፡

1. የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ እስከ ሐምሌ አምስት 2014 ዓ.ም. የኦዲት ግኝት ማስተካከያ የድርጊት መርኃ-ግብር አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ፤

2. ዩኒቨርሲቲው ተጠያቂነትን በሚያስከትሉ ጉዳዮች ላይ በርከኑ ርምጃ ወስዶ በአንድ ወር ጊዜ ሪፖርት እንዲያቀርብ፤

3. የመንግስት ግዢ እና ንብረት አገልግሎት በሺያጭ የሚወገዱትን አስወግዶ በሦስት ወር ውስጥ ሪፖርት እንዲያቀርብ፤

4. ዩኒቨርሲቲው ተመላሽ መደረግ የነበረበትን ሰባ ሚሊየን ብር አጽንዖት ሰጥቶ የማስመለስ ሥራውን እንዲሠራ፣ ከዚህ አንጻር ያሉ ሪፖርቶችንም በየሦስት ወሩ ሪፖርት እንዲያደርግ እና የበጀት አጠቃቀሙን እንዲያሻሽል፤

5. ዩኒቨርሲቲው ሕግ እና መመሪያዎችን አክብሮ ተልዕኮውን እንዲወጣ እና የኦዲት ግኝቱንም የዕቅዱ አካል አድርጎ እንዲሠራ፤

6. ከተማሪዎች ምገባ የዕለት ፍጆታ ተመን ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን የገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሁም የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ተገቢ የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲያቀርቡ፤

7. የገንዘብ ሚኒስቴር ተገቢውን ቁጥጥር አድርጎ፣ ከአመዘጋገብ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ዕልባት ሰጥቶ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሪፖርት እንዲያቀርብ የሚሉ ናቸው፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሠረት ዳምጤ፤ ተሰብሳቢ ሒሳቡ ከዓምናው መጨመሩን ጠቁመው፣ ትኩረት ሰጥቶ በወቅቱ መሰብሰብ እንዳለበት እና ተከፋይ ሒሳብም በወቅቱ መከፈል እንዳለበት አመልክተዋል፡፡ ተጠያቂነት ያለውን አሠራር መከተል እና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ የሚወገዱ ንብረቶችንም በአግባቡ ማስወገድ እና ጥቅም ላይ የሚውሉትንም ማዋል ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ የተማሪ ምገባን በሚመለከት መንግስት መፍትሄ ማበጀት እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር የኢንስፔክሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ አባይነሽ ተሾመ፤ አብዛኞቹ ግኝቶች የውስጥ ኦዲትን በአግባቡ ባለመጠቀም የሚመጡ በመሆናቸው፣ የወስጥ ኦዲትን እንደ ግብአት መጠቀም ይገባል ብለዋል፡፡ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር የኦዲት ዳይሬክተር ወይዘሮ አለሜ ኃይሉ በበኩላቸው፤ በዩኒቨርሲቲው ከ1 መቶ 81 ሚሊየን በላይ ጥቅም ላይ ያልዋለ ገንዘብ የተገኘው፣ በአግባቡ ካለማቀድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ገንዘቡን ሥራ ላይ ማዋል ካልቻለም፤ ሌላ በጀት ላነሳቸወ ተቋማት እንዲውል ቀድሞ ማሳወቅ እንደነበረበት ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ከማል አብዱራሂም (ዶ/ር) ደግሞ፤ የገቢ እና ወጪ፣ የተሰብሳቢ እና ተከፋይ ሒሳብን በሚመለከት ከቋሚ ኮሚቴው የቀረበላቸውን ጥያቄ መሠረት አድርገው ዝርዝር ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ አብዛኛዎቹ ግኝቶች ማስተካከያ የተደረገባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከተማሪ ምገባ ጋር ያለውን ግን በቀን አሥራ አምስት ብር የሚለው ውሳኔ አሁን ባለው ሁኔታ አሰቸጋሪ መሆኑን እና እገዛ እንደሚፈልጉ ተናገረዋል፡፡ የተሰጡ አስተያየቶችንም ወስደው በቀጣይ የሚሠሩባቸው መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

በ ፋንታዬ ጌታቸው