በሕዝብ ተወካዮች ክር ቤት የከተማ፣ መሠረተ-ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ በጅግጅጋ ከተማ እየተከናወነ ያለውን የመንገድ መሠረተ-ልማት አበረታታ፡፡

በፌዴራል መንግስት በጀት ከጅግጅጋ እስከ ሀርሙካሌ እና በሶማሌ ክልል በጀት በጅግጅጋ ከተማ እየተሠሩ ያሉ የውስጥ ለውስጥ የአስፋልት መንገዶችን ሰሞኑን ተዘዋውሮ የተመለከተው ቋሚ ኮሚቴው፤ ሥራዎቹ ይበል የሚያሰኙ ናቸው ብሏል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው አባል እና የመስክ ቡድኑ አስተባባሪ የተከበሩ አቶ ተሾመ ዋለ፤ በጅግጅጋ ከተማ እየተሠሩ ያሉ የውስጥ ለውስጥ የመንገድ መሠረተ-ልማቶች፣ የክልሉን ዕድገት ለማፋጠን እና የሕዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያግዛሉ ብለዋል፡፡

የተከበሩ አቶ ተሾመ አክለውም፤ የክልሉ አመራር ባሳየው ቁርጠኝነት እና ቅንጅታዊ አሠራር፤ የውኃ፣ የመብራት እና የቴሌኮሚዩኒኬሽን ተቋማት ተናብበው መሥራታቸውን በመልካም ጎኑ አንስተዋል፡፡ በአመራሩ በኩል፤ የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ  እየተኼደበት ያለው ርቀት የሚበረታታ መሆኑንም እግረ-መንገዳቸውን ጠቁመዋል፡፡

የተከበሩ አቶ ፈቃዱ ጋውሻሎ በበኩላቸው፤ የክልሉ መንግስት በክልሉ የሰፈነውን ሰላም ለማዝለቅ ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር፣ የሕዝቡን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ፍላጎት ለመመለስ ጠንክሮ ሊሠራ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር፤ በጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር፣ በክልሉ እና በፌዴራል መንግስት በጀት እየተሠሩ ያሉ የመንገድ መሠረተ-ልማቶች፤ በሲሚንቶ፣ ነዳጅ እና ፋይናንስ ዕጥረት እንዳይስተጓጎሉ፤ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት የተቀሩት የቋሚ ኮሚቴው አባላት አስገንዝበዋል፡፡

በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ፤ በከተማ ተቋማት እና መሠረተ-ልማት ማስፋፊያ ፕሮጄክት (UIIDP) ድጋፍ እና በሴፍቲኔት ፕሮጄክት እየተተገበሩ ያሉ የልማት ሥራዎች፤ ለሌሎች ክልሎች ኣርአያ ሊሆኑ እንደሚችሉ የቋሚ ኮሚቴው አባላት አክለው ተናግረዋል፡፡

ችግሮችን ለይቶ ማቀዱ አንዱ የመፍትሔው አካል መሆኑን የጠቆሙት የቋሚ ኮሚቴው አባላት፤ አመራሩ ችግሮችን ለመቅረፍ በዓለም ባንክ እንዲሁም በበከተማ ተቋማት እና መሠረተ-ልማት ማስፋፊያ ፕሮጄክት ድጋፍ፤ የከተማ ደረቅ ቆሻሻን በማስወገድ እና የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራሞችን በመተግበር፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም አድንቋል፡፡

የሶማሌ ክልል የከተማ፣ መሠረተ-ልማት እና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊው አቶ አብዱራህማን ኢድ በበኩላቸው፤ የቋሚ ኮሚቴው የምክር ቤት አባላትን የሕዝብ ውክልናን ለመወጣት ላደረጉት ኃላፊነት የተሞላበት የመስክ ምልከታ አመስግነዋል፡፡ አያይዘውም፤ የክልሉ መንግስት በመደበው 4 መቶ 07 ሚሊዮን ብር፣ የውስጥ ለውስጥ የአስፋልት መንገዶች በከተማው እየተሠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የጅግጅጋ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሻፊ አሕመድ ደግሞ፤ በክልሉ እና በፌዴራል መንግስት በጀት እየተሠሩ ያሉ መንገዶች በጥሩ አፈጻጸም መሆናቸውን ጠቁመው፤ በቀጣይ በፕሮጄክቶች የሚታዩ ክፍተቶችን በማረም፣ ዕቅዶችን ጭምር በመከለስ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ በትኩረት እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡

የሶማሌ ክልል የሥራ ዕድል ፈጠራ ቢሮ ኃላፊ አቶ ነስረዲን አሕመድ፤ ዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ መርኃ-ግብር ለሦስት ዓመታት የሚቆያ መሆኑን አስታውሰው፣ በአንደኛው እና በሁለተኛው ዙር በጅግጅጋ ከተማ በ30 ቀበሌዎች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚኖሩ ለ737 ወንዶች እና 1800 በላይ ለሚሆኑ ሴቶች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረበትም አስረድተዋል፡፡

በፕሮጄክቱ መጨረሻ እያንዳንዱ ተጠቃሚ በነፍስ-ወከፍ ራሱን እንዲያደራጅ የዓለም ባንክ 5 መቶ ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጹት ኃላፊው፤ ገንዘቡ ግን በቂ አይደለም ብለዋል፡፡

በጅግጅጋ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉ ዜጎችን በመለየት፣ የቁጠባ ባህልን በማሳደግ እና የግንዛቤ ሥራዎችንም ጭምር በመሥራት፤ ከዓለም ባንክ የተገኘው የገንዘብ ድጋፍ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል በትኩረት መሠራቱን አቶ ነስረዲን ገልጸዋል፡፡

የከተማውን ወጣቶች በምግብ ዝግጅት፣ በፀጉር ሥራ፣ በመንጃ ፈቃድ ስልጠና እና በከተማ ግብርና ሙያዎች በማሰማራት፤ በሕይወታቸው ለውጥ እንዲያመጡ ጥረት የተደረገ መሆኑንም፣ ኃላፊው አክለው አስረድተዋል፡፡  

በተሠራው ውጤታማ የሴፍቲኔት መርኃ-ግብርም፤ የሶማሌ ክልል ዕውቅና ማግኘት መቻሉን የቢሮ ኃላፊው አስታውሰዋል፡፡

መኩሪያ ፈንታ