(ዜና ፓርላማ)፣ ሰኔ 15፣ 2014 ዓ.ም፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብድር ፍትሀዊነትን እንዲያረጋግጥ አቅጣጫ አስቀምጧል።

ቋሚ ኮሚቴው የግሉን ሴክተር ብድር አቅርቦት፣ አጠቃቀም፣ አሰባሰብ እና አፈጻጸም ከፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ገምግሟል፡፡

ባንኩ በብድር ፖሊሲ መሰረት አሰራር ቢያዘጋጅም በየ ሶስት ዓመት ጊዜውን ጠብቆ ክለሳን የማያደርግ በመሆኑ በብድር ፖሊሲ፣ መመሪያ እና ህግን ባልተከተለ መልኩ አልፎ አልፎ የሚሰጥበት ሁኔታ መኖሩ በኦዲት መታየቱን የኮሚቴው አባላት አንስተዋል፡፡

ባንኩ ተበዳሪዎች ስለሚሰሩት ሥራ በጥልቀት የሚያሳይ የቢዝነስ እቅድ እና የቅኝት ጥናት ማስረጃ በሚገባ የማይገመግም መሆኑን የጠቀሰው ኮሚቴው፤ ከተበዳሪዎች ለማስያዣነት የቀረቡት ንብረቶች በአግባቡ እና በወቅቱ ለብድር ተመጣጣኝ የሆነ ማስያዣ ስለመቅረቡ ተጣርቶ መጽደቁን በተሟላ መንገድ የማያረጋግጥ መሆኑንም አንስቷል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስትያን ታደለ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስከ ሰኔ 22/2014 ዓ/ም ድረስ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ መርሃ ግብር ከኦዲት አንጻር የተገኙ ግኝቶች የሚስተካከሉበት እና ሥራዎች እንደሚስተካከሉ ግልጽ ሁነው ለራሳቸው ቋሚ ኮሚቴ፣ ለዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት እና ለፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መላክ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ሰብሳቢው አያይዘውም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኦዲት ግኝቶች አንጻር ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ጉዳዮችን ለይቶ በቂ የዕርምት እና የአስተዳደር ማስተካከያዎችን ወስዶ በ3 ወራት ጊዜ ሊያሳውቀን ይገባል ካሉ በኋላ የአሰራር መዛነፍ የፈጠሩ ባለሙያዎች እና የሥራ ሀላፊዎች ካሉ በተጨባጭ በስም ተጠቅሰው እርምጃ ተወስዶባቸው የእርምጃው አይነት ጭምር በ3 ወራት ጊዜ ውስጥ ሪፖርት ሊቀርብ ይገባል ብለዋል፡፡

ችግሩ የከፋ ከሆነ ይህንን ሪፖርት አይተን ተጨማሪ የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትሉ ጉዳዮች ካሉ አቅጣጭ እንደሚያስቀምጡ የተከበሩ አቶ ክርስትያን አስረድተው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የኦዲት ግኝቶችን መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማስተካከያዎችን ስለማድረጉ የማረጋገጫ ሪፖርት ለኮሚቴያቸው እና ለፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በየ 3 ወሩ እንዲያቀርብ እንጠይቃለን ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዘዳንት አቶ አቤ ሳኖ ባንኩ ታች ወርዶ ስለሚሰራ ግድፈቶች እና ድክመቶች ሊኖሩበት ስለሚችሉ ችግሮችን በሙሉ ወስደን በቀጣይ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል፡፡

የብድር ፍትሃዊነትም ለቀጣይ እርምት ስለሚጠቅም እንደ ግብዓት እንደሚወስዷቸው ተናግረው፤ በተለይ መረጃ አያያዝ ሥርዓት እንዲሁም ባንኩን ለማዘመን እና ችግሮችን ለማስተካከል ዓለም አቀፍ የጥናት አማካሪዎችን አምጥተናልም ብለዋል፡፡

በ መስፍን አለሰው