ኮርፖሬሽኑ ከ480 ሚሊዮን ብር በላይ የተገዛውን የማዳበሪያ ግብዓት ማስወገድ እንዳለበት ኮሚቴው አሳሰበ

(ዜና ፓርላማ)፣ ሚያዚያ 04፣2013 ዓ.ም.፣ በሕዝብ ተወካዮች ምር ቤት የገቢ፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዮች ቋሚ ኮሚቴ በግብርና ሚኒስቴር ትዕዛዝ በ 480 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የተገዛውን የማዳበሪያ ግብዓት ማስወገድ እንዳለበት አሳስቧል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው  ይህን ያለው ሰሞኑን የአዳማ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የማዳበሪያ ማከማቻን በአካል ተገኝቶ በጎበኘበት ወቅት ነው፡፡

በ2006 /2007 ዓ.ም. በጀት የተገዛው ፖታሽ፣ ዚንክ እና ሮን የተባሉ በድምሩ 332 ሺህ  623 ኩንታል የማዳበሪያ ግብዓት ጥቅም ላይ ሳይውል ተከማችቶ እንደሚገኝ ከኮርፖሬሽኑ የስራ ኃፊዎች ጋር በነበረው ውይይት መረዳት እንደቻለ የቡድኑ አስተባባሪ የተከበሩ አቶ አያሌው አይዛ ተናግረዋል ፡፡

ተከማችቶ ለሚገኘው እና አዲስ ለሚገባ ማዳበሪያ ለመጋዘን ኪራይ በዓመት 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር እንደሚከፈልም ቡድኑ ከተደረገለት ገለጻ መረዳቱን ነው አስተባባሪው የገለጹት፡፡

ጥቅም ላይ ሳይውል የቆየው የተከማቸ ማዳበሪያ ኮርፖሬሽኑ ለመሸጥ ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካ የገለጹት አቶ አያሌው፣ ክምችቱን ለማስወገድ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የበላይ የስራ ኃላፊዎች ጋር መወያየት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ከዚህ በፊት ከነበረው ተሻሽሎ ወቅቱን ጠብቆ ለአርሶ-አደሩ እየተሰራጨ መሆኑና ከወደብ ቀጥታ ወደ ክልሎች እንዲሄድ በመደረጉ አራት ቢሊየን ብር  ወጭ መቀነስ መቻሉን አስተባባሪው በጥንካሬ አንስተዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማሪያም በበኩላቸው ተከማችቶ የሚገኘው ማዳበሪያ ከመበላሸቱ በፊት በሽያጭ ለማስወገድ ጨረታ ቢወጣም ለጨረታ የቀረበው ዋጋ ኮርፖሬሽኑን  ለኪሳራ የሚዳርገው መሆኑን ጠቅሰው፣ ለክምችቱ እልባት ለመስጠት በቀጣይ ከግብርና ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ጋር እንደሚመክሩ ነው ያብራሩት፡፡

በፋንታዬ ጌታቸው