ከሶማሌ ክልል የተወከሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከህዝቡ የሚነሱ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

በተከበሩ አቶ ከማል ሀሺ የሚመራ ቡድን ከሱማሌ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ / አያን አብዲ መሀመድ እናክልሉ ምክር ቤት አባላት ጋር ህዝቡ በሚያነሳቸው የልማት ጥያቄዎች እና የተከሰተውን ድርቅ አስመልክቶ ከህዝቡ ጋር ለመነጋገር የሚያስችላቸውን ውይይት አካሂደዋል፡፡

በውይይቱም በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ለሚደረጉ የክትትልና የቁጥጥር ስራዎች እና  የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አዋጅን በተመለከተ ለሚደረጉ የህዝብ ውይይቶች በሚያስፈልጉቅድመ-ዝግጅት ስራዎች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

ክብርት አፈ-ጉባዔዋም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤት አባላት  በቅንጅት ህብረተሰቡን ለማወያየት ላሳዩት ተነሳሽንት አመስግነው አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የተከበሩ አቶ ከማል ሀሺ በበኩላቸው የክልሉ ምክር ቤት ለመስክ ስምሪቱ መሳካት ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀው የልማት ጥያቄዎች እንዲሁም በክልሉ የተከሰተውን ድርቅ በተመለከተ ከመረጣቸው ህዝብ ጋር በመወያየት ለሚነሱ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል ከሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል መንግስት አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ገልፀዋል።