(ዜና ፓርላማ)፤ ጥቅምት 8፣ 2015 ዓ.ም፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባው 4 ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለዝርዝር ዕይታ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

ምክር ቤቱ በቀዳሚነት ያየው ከጣሊያን መንግሥት የተገኘ ብድርን ለማጽደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1/2015 ሲሆን፤ በምክር ቤቱ ዋና የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር የተከበሩ አቶ ተስፋዬ በልጂጌ የብድር ስምምነቱ የጤና ዘርፉን ለማሻሻል እንደሚውል ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ ገለጻ ባደረጉበት ወቅት ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት የነበሩት የብድር ስምምነቶች ምን ያክል ውጤታማ እንደነበሩ እንዲሁም አሁን ባለው ወቅታዊ ችግር የእናቶችና ህጻናት ጤና አስቸጋሪ ደረጃ ላይ በመድረሱ ለዝርዝር እይታ የተመራለት ቋሚ ኮሚቴ በትኩረት ሊመለከተው እንደሚገባም የምክር ቤቱ አባላት አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

ሥርዓተ-ምግብን ለማሻሻል ከዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት የቀረበ የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 2/2015ን በሚመለከት በምክር ቤቱ ዋና የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር አጭር ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን፤ የፕሮግራሙ ዓላማ የሀገሪቱን ስርዓተ ምግብ ማጠናከርና ማሻሻል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ በብድር ስምምነቱ ታሳቢ ቢደረግ፤ እንዲሁም ፕሮጀክቱ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ክትትል ማድረግ እንደሚገባ በምክር ቤቱ አባላት ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

በሌላ በኩል የብሔራዊ ክፍያ ሥርዓትን ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ አዋጅ እንዲሁም የመንግሥት እና የግል አጋርነት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጆች የቀረቡ ሲሆን፤ በመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ አማካይነት የአዋጆቹን አስፈላጊነት በሚመለከት ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በተለይ የመንግሥት እና የግል አጋርነትን የሚመለከተው አዋጅ አብሮነትን ለማጠናከር፣ ተባብሮ መስራትን ለማበረታታት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የምክር ቤቱ አባላት የተናገሩ ሲሆን፤ ለሀገር ውስጥ አጋርነት ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት የመረመራቸውን አራት ረቂቅ አዋጆች ለዝርዝር ዕይታ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ የመራ ሲሆን፤ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ በዛሬው መደበኛ ስብስባ የተያዙ ሌሎች አጀንዳዎች በቀጣይ መደበኛ ጉባኤ እንደሚታዩ ጠቁመዋል።

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት

በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament

በዩቲዩብ https://www.youtube.com/watch?v=cp_8F5TEeFE

በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews

በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr

በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ