(ዜና ፓርላማ)፤ ሰኔ 21፣ 2014 ዓ.ም.፤ ባሌ፤ የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ ለድርቅ ተጎጂዎች የሚቀርበው እርዳታ ከተጎጂዎቹ ቁጥር ጋር አለመመጣጠኑን በጉዳቱ ስፍራ ባካሄደው የመስክ ምልከታ አረጋገጠ።

ኮሚቴው ይህንን ያረጋገጠው፤ በምሥራቅ ባሌ ዞን በራይቱ እና ሶዌና ወረዳዎች በድርቅ የተጎዱ የሕብረተሰብ ክፍሎች ያሉበትን ሁኔታ እንዲሁም እየቀረበ ስላለው ድጋፍ በአካል ተገኝቶ ከተመለከተ በኋላ፤ ከኃላፊዎች፣ ከተጎጂዎች ተወካዮች እና ከሰነዶች ባገኘው መረጃ መሠረት ነው።

የኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር)፤ ቡድኑ በአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በኩል ለተጎጂዎች እየቀረበ ያለውን ርዳታ የሚያደንቅ ቢሆንም፣ ድጋፉ ከተጎጂው ቁጥር ጋር የማይመጣጠን መሆኑን መረዳታቸውን ተናግረዋል፡፡ ለችግሩ መንግስት ትኩረት እንደሚሰጠው እና በቀጣይም ኮሚቴው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡

አክለውም፤ የሁለቱን ወረዳዎች የሥራ ኃላፊዎች እና የድርቅ ተጎጂዎቹን ተወካዮች ባነጋገሩበት ወቅት፤ ትርፍ አምራች እና እንግዳ ተቀባዩ የባሌ አካባቢ በድርቅ በመጎዳቱ ርሳቸው እና የቡድናቸው አባላት ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

የኮሚቴው አባል የተከበሩ ወይዘሮ ፋንታዬ ለገሰ በበኩላቸው አካባቢው ለሌሎች የሚተርፍ ዕምቅ ሀብት ያለው ሆኖ ሲያበቃ፤ አልፎ አልፎ በሚከሰተው ድርቅ እና መንገድን ጨምሮ ሌሎች መሠረተ-ልማቶች ባለመሟላታቸው ወደ ኋላ መቅረቱን ጠቁመው አውስተዋል። ኮሚቴውም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የመፍትሔው አካል ለመሆን የራሱን ጥረት እንደያሚደርግም አመልክተዋል፡፡

በምልከታው ወቅት የራይቱ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኢብራሂም ረሺድ እና የሶዌና ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሳምሶን አበበ በወረዳዎቹ ስለተከሰተው የድርቅ አደጋ ሁኔታ እና እየቀረበ ስላለው ርዳታ ለኮሚቴው አባላት አጠቃላይ መረጃ ሰጥተዋል፡፡

የሚፈለገው እርዳታ እና የሚቀርበው የርዳታ መጠን ከተረጂው ቁጥር ጋር ያለመጣጣም፣ የመንገድ ችግር እና አካባቢው ጠረፋማ በመሆኑ ከድንበር ጋር ተያይዞ አልፎ አልፎ የሚነሱ ግጭቶች ርዳታ በማድረሱ ሂደት ላይ እንቅፋት መፍጠራቸውን ሁለቱም ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

የድርቁ ተጎጂዎች ተወካዮች በበኩላቸው በቂ ርዳታ የማይቀርብላቸው ከመሆኑም ባሻገር፤ ከፍተኛ የመንገድ እና የውኃ ችግር እንዳለባቸው ለኮሚቴው አስረድተዋል፡፡

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አማካሪ አቶ አበበ አባቡልጉ፤ ኮሚሽኑ በዞኑ ለተከሰተው የድርቅ አደጋ ድጋፍ እያደረገ ቢቆይም፣ በዚህ ምልከታ ግን ከሕዝቡ ቁጥር ጋር የማይመጣጠን መሆኑን ማረጋገጥ መቻላቸውን ተናግረዋል። በቅርቡ ኮሚሽኑ ከተረጂው ቁጥር ጋር የሚመጣጠን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡

በሁሉም ወረዳዎች ከሥራ ኃላፊዎች እና ከተጎጂ ተወካዮች ጋር የተደረገው ውይይት፤ በአካባቢው ባሕል መሠረት በሀገር ሽማግሌዎች ምርቃት ተጀምሮ እንደዚያው በምርቃት ተጠናቅቋል፡፡

በተያያዘ ዜናም የኮሚቴው አባላት በራይቱ ወረዳ በ2012 ዓ.ም. የተጀመረውን የጨልጨል ግድብ የጎበኙ ሲሆን፤ በጉብኝቱ ወቅትም የኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) በዝናብ ዕጥረት ሳቢያ በተደጋጋሚ ድርቅ በሚመላለስባቸው ቆላማ አካባቢ ለሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለከብቶቻቸው እና ለእርሻ ሥራቸው ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለውን ይህን መሰል ግድብ መገንባቱ ዘላቂ መፍትሔ ይሆናል ብለዋል። ስለሆነም ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ግድቡን ማጠናቀቅ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

በ ኃይለሚካኤል አረጋኸኝ