(ዜና ፓርላማ)፤ ጥቅምት 5፣ 2015 ዓ.ም.፤ የምክር ቤቶች የስራ እንቅስቃሴ በውጤት የታጀበ እና የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የመለሰ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚገባ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ አስገነዘቡ።

አፈ-ጉባዔው ይህን ያሉት በጅማ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የሀገር አቀፍ ህግ አውጪዎች የጋራ የምክክር መድረክ ላይ የቀረበውን የክልል ምክር ቤቶች የ2014 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ካዳመጡ በኋላ ነው።

በዚሁም ወቅት ምክር ቤቶች የሀገር ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ለዴሞክራሲ ስርዓት መስፈን ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት አፈ-ጉባዔው፤ በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች ተግባሮቻቸውን ሲያከናውኑ የሕዝብን ጥያቄ የመለሰና ተጠያቂነትን ያረጋገጠ መሆኑን ማጤን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ክልሎች ምክር ቤቶቻቸውን ለማጠናከርና ምቹ የስራ አካባቢ ለመፍጠር የጀመሩትን ተግባር አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የጠቆሙት አፈ-ጉባዔው፤ ምክር ቤቶቹም ያቀረቡት የአፈጻጸም ሪፖርት ከክልል ክልል ቢለያይም ሁሉም ስራ ላይ መሆናቸውን የሚያመላክት እና እርስ በእርሳቸውም ልምድ የተለዋወጡበት በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው፤ በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች የሕዝብ ሉአላዊነት መገለጫ መሆናቸውን በተግባር ማስመስከርና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጡ መሆን እንዳለባቸው በአጽንኦት አንስተዋል።

ምክር ቤቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ካስፈለገ የበጀት ነጻነታቸው መረጋገጥ አለበት ያሉት የተከበሩ አቶ አገኘሁ በፌደራል ደረጃ ያሉት ሁለቱ ምክር ቤቶች ከጠነከሩ የታችኞቹን ምክር ቤቶች ማጠናከር እንደሚቻልና ለተግባራዊነቱም ሁሉም የየድርሻው ሊወጡ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።

አክለውም የሁለቱ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤቶችም ራሳቸውን በእውቀት አደራጅተው የምክር ቤቶቹን ክብርና ሞገስ በማስጠበቅ ለስራዎቻቸው ምቹ ሁኔታ መፍጠር ቁልፍ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል ሲሉም አስታውሰዋል።

ተሳታፊዎች በበኩላቸው መድረኩ የምክር ቤቶቹ አፈጻጸም ያለበትን ደረጃ ከማሳየቱም ባሻገር ጠቃሚ የእርስ በእርስ ልምድ ልውውጥ የተገኘበት በመሆኑ በቀጣይም ሁለቱ የፌደራል ምክር ቤቶች ለታችኞቹ ምክር ቤቶች የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ብለዋል።

በ ድረስ ገብሬ

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት

በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament

በዩቲዩብ https://www.youtube.com/watch?v=cp_8F5TEeFE

በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews

በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr

በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ