በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የሶማሌ ክልል በእንስሳት ሀብት አያያዝ እና አስተዳደር ረገድ በርካታ ችግሮች እንደተጋረጡበት ተገነዘበ፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ቡድን በክልሉ ሰሞኑን ባደረገው የመስክ ምልከታ፤ የእንስሳት ማቆያ ስፍራዎችን ወቅታዊ ሁኔታ፣ ከእንስሳት ጋር የተያያዙ የግንባታ ማዕከላት፣ ድርቁ በእንስሳት ላይ ያስከተለውን ጉዳት፣ በእንስሳት ዘርፍ የተደረጉ ድጋፎችን እና ከሕገ-ወጥ የእንስሳት ዝውውር በተያያዘ የሚስተዋሉትን ዕጥረቶች ተረድቷል፡፡

ቡድኑ በቅድሚያ የጎበኘው በ54 ነጥብ 6 ሄክታር ላይ ግንባታው ተጀምሮ የተቋረጠውን የጅግጅጋ የእንስሳት ማቆያ ማዕከል ሲሆን፤ ግንባታው ሕገ-ወጥ የእንስሳት ዝውውርን በመቀነስ፣ የእንስሳት የወጪ ንግድን ለመጨመር ያለመ ነበር፡፡ ግንባታው የተጀመረው በግብርና ሚኒስቴር እና በቀድሞው አጠራር የግብርና እና ገጠር ልማት በተሰኘው የክልሉ ቢሮ በ2005 ዓ.ም. በ86 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ከክልሉ አርብቶ-አደር ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ፕሮጄክቱ በበጀት ዕጥረት ተገቢው ክትትል እና ድጋፍ ስላልተደረገለት የተጀመረው ግንባታ መፈራረስ መጀመሩን ቋሚ ኮሚቴው በአካል አረጋግጧል፤ ለክልሉ አርብቶ-አደር ቢሮ የእንስሳት መኖ ዳይሬክቶሬትም አስረድቷል፡፡

ኮሚቴው በአርቲሼክ ቀበሌ የቁም እንስሳት የግብይት ማዕከል ተገኝቶ እንደተመለከተው፤ በግ እና ፍየል እየቀረቡ ቢሆንም፣ በድርቁ ምክኒያት ግን የቀንድ ከብቱ አቅርቦት ተቀዛቅዟል፡፡ በድርቁ የተጎዱ እንስሳትም ለገበያ እየቀረቡ መሆኑን ኮሚቴው ታዝቧል፡፡

በግብይት ማዕከሉ ለእንስሳት አገልግሎት የሚሰጡ ጊዜያዊ መጠለያ፣ የውኃ እና የእንስሳት መኖ ማቅረቢያ ግንባታዎች ስላልተዘጋጁላቸው፤ በእንስሳቱ ግብይት ላይ ተጽዕኖ እየተፈጠረባቸው መሆኑን ግብይት ላይ የነበሩት አርብቶ-አደርች ለኮሚቴው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በመሮጋጆ ቀበሌ በመገኘት፤ በድርቅ ምክኒያት የደረሰውን ጉዳት እና እየተደረገ ያለውን ድጋፍ ኮሚቴው ተመልክቷል፡፡ በወቅቱም ለእንስሳት በቂ መኖ እና የውኃ አቅርቦት ባለመኖሩ፣ ብዛት ያላቸው እንስሳት ለጉዳት መዳረጋቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኮሚቴው አብራርተዋል፡፡

በድርቁ ምክኒያት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው መቅረታቸውን፤ ጉዳቱ ከፍተኛ ቢሆንም፣ ለአካባቢው ከፊል አርብቶ-አደር ነዋሪዎች የሚደረገው ድጋፍ ግን ዝቅተኛ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ለመረዳት ችሏል፡፡

ሕገ-ወጥ የእንሳስት ዝውውርን እና ንግድ በተመለከተ፤ ከሚመለከታቸው አመራሮች ጋር ተወያይቷል፡፡ ክልሉ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚዋሰን በመሆኑ፤ ሕገ-ወጥ የእንስሳት ዝውውር በከፍተኛ ደረጃ ይታያል ያለው ቋሚ ኮሚቴው፤ ለዚህም ኃላፊነት ወስዶ የሚሠራው ግብረ-ኃይል ሥራውን በአግባቡ አለመወጣቱን ኮሚቴው ተገንዝቧል፡፡

የኮሚቴው ቡድን አስተባባሪ የተከበሩ አቶ እንዳልካቸው አሥራት፤ በክልሉ ትኩረት በሚያሻቸው ጉዳዮች ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና ባለሙያዎች ተወያይተው የጋራ አቋም መያዝ አለባቸው ብለዋል፡፡

የተከበሩ እንዳልካቸው አክለውም፤ በክልሉ የእንሳሳት ማቆያ ግንባታ፣ በድርቁ ዙሪያ እና በሕገ-ወጥ የእንሳሳት ዝውውር እና ንግድ ረገድ ሰፊ ውይይት በማድረግ፤ የተጀመሩትን ግንባታዎች ለመጨረስ እና ለሌሎችም ጋሬጣዎች መፍትሔ ለማፈላለግ፣ የፌዴራል እና የክልሉ መንግስታት፣ በጥናት ላይ የተመረኮዙ አማራጮችን ማምጣት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

“ድርቅ ለተከሰተባቸው አከባቢዎች ዕኩል ትኩረት በመስጠት፤ ውኃ እና የእንስሳት መኖ የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት፣ ሕገ-ወጥ የእንስሳት ግብይትን ለመቆጣጠር የክልሉን ግብረ-ኃይል ማጠናከር እና በየጊዜው የሥራውን ሂደት በመገምገም ችግሩን በተገቢው መንገድ መፍትሔ ማፈላለግ ያሻል” አስተባባሪው እንዳሉት፡፡

የሶማሌ ክልል አርብቶ-አደር እንስሳት መኖ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መሐመድ በዲል በበኩላቸው፤ ኮሚቴው እንድናስተካክል የጠቆመንን ጉድለቶች የቀጣይ ዕቅዳችን አካል አድርገን እንሠራልን ካሉ በኋላ፣ የክልሉን የድርቅ መባባስ ሁኔታ የፌዴራል መንግስት በልዩ በትኩረት ሊያየው ይገባል ብለዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለውም፤ የገበያ ማዕከላት ላለፉት አምስት ዓመታት ጥገና ስላልተደረገላቸው፤ ከክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመወያየት፣ ችግሩ በአፋጣኝ ተፈትቶ የአካባቢውን ማኅበረሰብ የሚመጥን የገበያ ማዕከል ይሠራል ብለዋል፡፡