(ዜና ፓርላማ)፣ ጳጉሜ 2፣ 2014 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ሴቶች በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፍ ላይ ተሳታፊና ውሳኔ ሰጪ እዲሆኑ ለማስቻል የኮከሱ አመራሮች ልምድ ልውውጥ አድርገዋል፡፡

የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ሴት ተመራጭ ኮከስ አመራሮች ከኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኮከስ አመራሮች ጋር ዛሬ ባደረጉት ልምድ ልውውጥ የምክር ቤቱ ኮከስ አመሰራረት፣ አደረጃጀት፣ የበጀትና መሰል መዋቅራዊ ሂደቱ እንዴትና በምን መልኩ እየሄደ እንደሆነና የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ኮከስም አዲስ እንደመሆኑ መጠን በምን ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንዳለበትም ምክር ጠይቀዋል፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሴት ተመራጭ ኮከስ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ኪሚያ ጁንዲ በምክር ቤቶቹ በሚሰሩ ስራዎች ላይ የሴት ተመራጮችን ሚና ለማጎልበትና በተለይ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ምክር ቤታዊ በሆኑ ስራዎች ላይ በብቃት እንዲሳተፉ ለማስቻል እንደዚህ አይነት የእርስ በርስ ልምድ ልውውጥ ከፍተኛ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡

የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ምስራቅ መኮንን በበኩላቸው የክልል ምክር ቤት በባህሪው ከፌደራል የተለየና በስፋት ከመረጠው ህብረተሰብ ጋር የመገናኘት፣ አብሮ የመስራት እና በቅርበት ችግሮችን አይቶ የመፍታት እድሉ ሰፊ በመሆኑ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በምክር ቤቱ በኩል ለማረጋገጥ የኮከሱን አባላት የማብቃት ስራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

ምክር ቤቱ በሚሰራቸው ህግ በማውጣት፣ በሕዝብ ውክልና እንዲሁም በክትትልና ቁጥጥር ስራዎች ሴቶች ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ኮከስ ድርሻው የጎላ በመሆኑ የኮከሱ አባላት በብቃትና በንቃት እንዲሳተፉ የአቅም ግንባታ ስራዎች ተሰርተዋል፤ በኮከሱ አደረጃጀትም መዋቅራዊ ሂደት ውስጥ ተመራጭ የሆኑ ሁሉም ተሳትፎ እንዲኖር ህብረ ብሄራዊነትን ለማስጠበቅ እንደተሞከረ የገለጹት በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኮከስ ጸሐፊ የተከበሩ ዶ/ር ቢፍቱ መሀመድ የክልሉ ምክር ቤት ኮከስም ከዚህ ልምድ ሊወስድ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የተከበሩ አስቴር ከፍታው አሁን ላይ በምክር ቤቱ ያሉት የኮከስ አባላት በብዛት አዲስ እንደመሆናቸው መጠን ኮከሱ ለምን አላማ እንደተቋቋመ አባላቱ እንዲገነዘቡ የማድረግ ስራ በስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ በክልሉ ምክር ቤትም ይህ አይነት የግንዛቤ ስራ ቢሰራ አባላትን ለማጠናከር ወሳኝነት እንዳለው እና ለተቋቋመለት አላማ እንዲቆሙም ያደርጋልም ብለዋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የሴቶች እና ህጻናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ነጭቴ ፍላቴ በምክር ቤቱ ኮከስ በህጋዊነት የተቋቋመው ከ3ተኛው ዙር ምክር ቤት ጀምሮ መሆኑን አብራርተው ኮከሱ ከጊዜ ወደ ጉዜ እያደገ እና ራሱን እያደራጀ የራሱ አደረጃጀትና አሰራር ደንብም ጭምር እንዳለው እና አሁን ላይ አባላቱ 196 መድረሳቸውን ነው የገለጹት፡፡

የሁለቱ ምክር ቤት ኮከሶች በቀጣይ በተጠናከረ መልኩ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የእርስ በእርስ ግንኙነቱን ማጠናከር አስፈላጊ እንደሆነና በተለይም የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ኮከስ ራሱን በሁሉም ዘርፍ ለማሳደግና ለማደራጀት በሚያደርገው ጥረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኮከስ ከጎኑ እንደሚቆምም አመራሮቹ አረጋግጠውላቸዋል።

በ ኢያሱ ማቴዎስ

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት

በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament

በዩቲዩብ https://www.youtube.com/watch?v=cp_8F5TEeFE

በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews

በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr

በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ