የተቋረጠው የሐዋሳ ስቴዲዬም ግንባታ እንዲቀጥል ኮሚቴው አሳሰበ

(ዜና ፓርላማ)፤ መጋቢት 2013 ዓ.ም.፣ ሐዋሳ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የተቋረጠው የሐዋሳ ስቴዲዬም ግንባታ እንዲቀጥል አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ይህንን ማሳሰቢያ የሰጠው፤ ሰሞኑን በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሐዋሳ ከተማ የመስክ ምልከታ በአካሄደበት ወቅት ነው፡፡ የግንባታውን አሁናዊ ይዞታ የገመገመው የስቴዲዬሙ ግንባታ የቴክኒክ ኮሚቴ፤ ከዐቢይ ኮሚቴ በሚሰጠው አቅጣጫ ተመሥርቶ ወደ ግንባታ ለመግባት የሚያስችለውን ሁኔታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንዲያመቻችም የቋሚ ኮሚቴው ቡድን ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ሞሚና መሐመድ አመላክተዋል፡፡  

የሐዋሳ ስቴዲዬም ግንባታ የመጀመሪያ ምዕራፍ የተጠናቀቀ ቢሆንም፤ ለአደጋ ተጋልጦ  አገልግሎት ሳይሰጥ መቀመጡ ተገቢ ባለመሆኑ ለችግሩ መፍትሄ ሊበጅለት እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡ በተጨማሪምስፖርቱ ዘርፍ ጋር ተያይዞ ጤናማ እና ብቁ ዜጎችን ለማፋራት የስፖርት ማዘዉተሪያዎች ትልቅ ሚና ስላላቸዉ በቂ ትኩረት ለዘርፉ እንዲቸርም ኮሚቴው አያይዞ አስገንዝቧል፡፡

የሐዋሳ ዓለም-አቀፍ ስቴዲዬም ሳትኮን ከተሰኘ ሀገር-በቀል የግንባታ የግል ኩባኒያ ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት በ7 መቶ ሚሊዬን ብር የተገነባ ሲሆን፤ የመጀመሪያ የግንባታ ምዕራፉን በውሉ መሠረት ማጠናቀቁን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እናም የሲዳማ ክልል የባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃጎ አገኘሁ፤ ስቴዲዬሙ እስካሁን ርክክብ የአልተደረገለት በመሆኑ የፌዴራል መንግስትን ምላሽ እንደሚፈልግ ጠቁመዋል፡፡

የሲዳማ ክልል ዕምቅ የባህል እና የቱሪዝም ሀብት ባለቤት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፤ በክልሉም ሆነ በባሕል እና ቱሪዝም ኒስቴ ጥናቶች በማድረግ እና የዓቅም ግንባታ ድጋፍ በመስጠት በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አመላክቷል፡፡

የክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የክልሉን ብሔረሰብ ቋንቋ ለማሳደግ በክልሉ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ለሚገኙ ሠራተኞች የቋንቋው ስልጠና እየሰጠ እንደሆነ ቋሚ ኮሚቴው ከተደረገለት ማብራሪያ ተረድቷል፡፡ በክልሉ የነበረው የጸጥታ ችግር ተቀርፎ ባሕል እና ቅርስ የማስተዋወቅ ሥራው በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት በመሠራቱ የቱሪስቶች ቁጥር እየጨመሩ መምጣቱን ኮሚቴው ከክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የማኔጅመንት ቡድን ጋር ካካሄደው ውይይት መረዳቱን ተናግሯል፡፡

የሲዳማ ክልል ቱሪዝም ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ሳሙኤል በላይነህ እንደሚሉት፤ በ2012 የበጀት ዓመት ክልሉን ይጎበኛሉ ተብለው የተጠበቁት ቱሪስቶች 1 ነጥብ 6 ሚሊዬን ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጽዕኖ እና መጠነኛ የፀጥታ ችግር ባለበት ሁኔታ፤ በበጀት ዓመቱ 9 መቶ ሺህ ቱሪስቶች ክልሉን መጎብኘታቸውን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በ መስፍን አለሰው