(ዜና ፓርላማ)፤ ሰኔ 15፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የፌዴራል ኦዲተር ጄኔራል ቢሮ፤ ለማከናወን ያቀዳቸውን 29 የፌዴራል መንግስት መሥሪያ ቤቶችን የ2013 በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት ሥራ ማጠናቀቁን ገለጸ።

ሥራው በዕቅዱ መሠረት መከናወኑን ለኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች 6ኛው ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 15ኛ መደበኛ ጉባዔ የገለጹት፤ የፌዴራል ኦዲተር ጄኔራል ወይዘሮ መሠረት ዳምጤ ናቸው፡፡

"በክዋኔ ኦዲቱ ላይ ትኩረት በማድረግ፤ ባስቀመጥነው አቅጣጫ መሠረት በመንግስት መሥሪያ ቤቶች የተቀረጹ ኘሮግራሞች እና ኘሮጄክቶች፤ እንዲሁም ለተልዕኮ ማስፈጸሚያ የተመደበላቸውን በጀት በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋላቸውን እና የታለመላቸውን ዓላማ እና ግብ በብቃት እና ስኬታማ በሆነ መንገድ ማሳካታቸውን እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ እና የዘላቂ ልማት ግቦችን ሊያሳካ በሚችል መልኩ ማከናወናቸውን ለማረጋገጥ ተንቀሳቅሰናል" ብለዋል ዋና ኦዲተሯ፡፡

በሌላ በኩል በኦዲቱ የታዩትን እና የምክር ቤቱን ትኩረት የሚሹ ዋና ዋና ግኝቶቹንም ለምክር ቤቱ አብራርተዋል፡፡ ከእነዚህም ወስጥ የአዳማ የግብርና ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ያለምንም የግዢ እና የገበያ ፍላጎት ጥናት ስለፈጸማቸዉ ግዢዎች የተወሰደውን የኦዲት ግኝት ገልጸዋል፡፡

የተቀናጀ መሰረተ-ልማት ከማከናወን ረገድ፤ የልማት ሥራዎች የከተሞችን ማስተር ፕላን (የከተሞችን መሠረተ-ልማት ስታንዳርድ (መንገድ፣ ውኃ፣ መብራት) መሠረት አለማድረግ፣ የከተሞች ማስተር ፕላን ሲዘጋጅ መንገድን ብቻ መሠረት ያደረገ መሆኑ እና ሌሎች መሠረተ-ልማቶችን አለማካተቱ፣ እንዲሁም ሀገራዊ የመሠረተ-ልማቶች የዕድገት አቅጣጫ አለመኖሩን ክብርት ወይዘሮ መሠረት አስረድተዋል፡፡

ዋና ኦዲተሯ በሪፖርታቸው ካነሷቸው የኦዲት ግኝት ተቋማት የአዳሚ ቱሉ ፀረ-ተባይ ፋብሪካን ነው። ፋብሪካው ግዢ ሲፈጽም ጥቅም ላይ የሚያውላቸውን፣ የሚያሠራጫቸውን በአጠቃላይ ለአገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎችን እና ምርቶችን ከአቅራቢዎች ከመገዛታቸው በፊት አካባቢን የማይበክሉ ስለመሆናቸው የሚያረጋግጥበት ሥርዓት ያልዘረጋ መሆኑን፤ ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሠረት ዳምጤ አመልክተዋል፡፡

የክዋኔ ኦዲት ሪፖርቶች፤ ጉድለቶችን ከማሳየት ባሻገር የታዩ የአሠራር ጉድለቶችን እና ክፍተቶችን ማረም እና ማስተካከል የሚያስችል የመፍትሔ ሐሳቦችን ጭምር ያካተቱ ከመሆኑም በላይ፣ አብዛኛዎቹ የተሰጡት የማሻሻያ ሐሳቦች በኦዲት ተደራጊዎችም ጭምር ከስምምነት የተደረሰባቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩልም፤ በበጀት ዓመቱ በተለያዩ ጉዳዮች በተደረጉ የክዋኔ ኦዲቶች፣ በርካታ ሊዘረጉ የሚገቡ የአሠራር ሥርዓቶች መኖራቸው መረጋገጡንም ገልጸዋል።

የየመሥሪያ ቤቶቹን ቅልጥፍና እና ውጤታማነት የሚያደናቅፉ፣ እንዲሁም ለተልዕኮ ስኬት አለማማር አስተዋጽዖ የነበራቸው የሕግ እና የአሠራር ሥርዓቶች እንዲሁም ተዘርግተዉ የማይተገበሩ የአሠራር ሥርዓቶች፤ በመሥሪያ ቤት ውስጥም ሆነ ከሌሎች ተቋማት ጋር የቅንጅት እና የትብብር ጉድለቶች ዐበይት ግድፈቶች መሆናቸውንም ዋና ኦዲተሯ አስገንዝበዋል፡፡

በ አትጠገብ ቸሬ