(ዜና ፓርላማ)፣ ነሐሴ 21፣ 2014 ዓ.ም፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከሃገር አቀፍ ፈተናዎች አገልግሎት የሥራ ሀላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እያደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን ገልፀው፤ ውጤታማነቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

በመድረኩ ላይ የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና አሰጣጥ ዝግጅት፣ የዩኒቨርስቲ ተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና አሰጣጥ፣ የትምህርት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ተቋማዊ ሪፎርም፣ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ (autonomous) ለማድረግ ስለተያዘው ዕቅድ እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመልካም አስተዳደር ችግሮች በዋናነት ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ በስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድን ከመገንባት አኳያ በትምህርት ሚኒስቴር የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራና ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ስለመኖራቸውም ተብራርቷል።

ቋሚ ኮሚቴው የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተናን በሚመለከት ከወላጆች የሚነሱ ስጋቶችን እና ጥያቄዎችን እንዲሁም፤ ከየክልሉ ትምህርት ቢሮዎች ያሰባሰባቸውን መረጃዎች መሰረት በማድረግ ጥያቄዎችን ያቀረበ ሲሆን፤ በስራ ኃላፊዎቹ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡

የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ማንደፍሮ (ዶ/ር) የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልፀው፤ የ2014 ዓ/ም የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና አሰጣጥ በተሳካ ሁኔታ ለማጠናቀቅ ከሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል መንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር በቅንጅት ዘግጅት እየተደረገ መሆኑን ተነናግረዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ተፈታኞች የልፋታቸውን ውጤት ብቻ የሚያገኙበት እንዲሆን እንደከዚህ በፊቱ ለማንም የፖለቲካ አጀንዳ እንዳይሆን ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የትምህርት ሚኒስትርና የዩኒቨርስቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢዎች እና አባላትን ጨምሮ የተጣለባቸውን ሃላፊነት በአግባቡ መወጣታቸውን በቀጣይ የቋሚ ኮሚቴው ጥብቅ ክትትል ያደረጋል ብለዋል።

ዩኒቨርስቲዎቻችን የመልካም አስተዳደር ተምሳሌት ሊሆኑ እንደሚገባና ከፕሬዚዳንቶች ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የስራ ሀላፊዎች ዋና ዋና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ማህበረሰቡን በንቃት እንዲያገለግሉ ዶ/ር ነገሪ አሳስበዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ም/ሰብሳቢ የተከበሩ ዶ/ር ከይረዲን ተዘራ በበኩላቸው የትምህርት ዘርፍ የነገውን ሀገር ተረካቢ ትውልድ ህይወት የሚቀረፅበት በመሆኑ በጥንቃቄ ሊመራ ይገባል ብለዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ችግሮችን በተለይ አገራዊ ጉዳዮችን ለመፍታት ከቋሚ ኮሚቴው ጋር በጋራ እንደሚሰሩ አስገንዝበው፤ በቋሚ ኮሚቴው የተቀመጡትን አቅጣጫዎች ተቀብለው በቀጣይ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩበት ተናግረዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በ2014 ዓ/ም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መልሶ ሲደራጅ ጀምሮ ካካተታቸው ዋና ዋና የሪፎርም አጀንዳዎች መካከል የመውጫ ፈተናን በሚመለከት አመቱን ሙሉ በጥናት ላይ የተደገፉ ውይይቶች መደረጋቸውን ጠቁመዋል።

ሚኒስቴር ዴኤታው አክለው መውጫ ፈተናው ለትምህርት ጥራት ስብራትን ለመጠገን ከሌሎች የመፍትሄ አቅጣጫዎች ጋር ተደምሮ ውጤት ሊያስገኝ እንደሚችል ገልፀው፤ መውጫ ፈተናው ከ2015 ዓ.ም ምሩቃን ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በ መስፍን አለሰው

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት

በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament

በዩቲዩብ https://www.youtube.com/watch?v=cp_8F5TEeFE

በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews

በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr

በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ