(ዜና ፓርላማ)፣ መስከረም 4፣ 2015 ዓ.ም.፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመሬት ወረራና በፀጥታ ስራ ላይ ትኩረት መስጠት እንዳለበት ከአዲስ አበባ የተመረጡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጠቁመዋል፡፡

አባላቱ ዛሬ ከከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በአስተዳደሩ በተከናወኑ ተግባራትና በሕዝብ እየተነሱ ባሉ ጥያቄዎች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

በዚሁም ወቅት ከተማ አስተዳደሩ ሕዝቡ የሚያነሳውን የኑሮ ውድነት ለማቃለል እያደረገ ያለው የምገባ ስርዓት፣ ሰላምና ፀጥታ ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት፣ የግንባታ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም፣ የአካባቢ ፅዳትና ውበት አፈፃፀም ላይ እያከናወናቸው ያሉትን ተግባራት በአዎንታዊ ያነሱት አባላቱ አሁንም በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በኑሮ ውድነት፣ በግንባታ አቅርቦት እንዲሁም በመሬት ወረራና በፀጥታ ችግር ዙሪያ አመራሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አመላክተዋል።

የከተማው ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው በየደረጃው ያለው አመራር እስከታችኛው መዋቅር ድረስ በተለያዩ ጊዜያት በመውረድ ከሕዝቡ ተቀራርቦ እንዲሰራ ለማድረግ ዕቅድ መያዙን ጠቁመው ከተማ አስተዳደሩ ከነዋሪው ለተነሱ ጥያቄዎች በየደረጃው መልስ እየሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።

አባላቱ በቀጣይ ከሕዝብ በሚያደርጉት ውይይት የሚነሱ ጥያቄዎችንና ሀሳቦችን ለመመለስ ከተማ አስተዳደሩ በሁሉም መዋቅር ግብረ-መልሶቹን የዕቅዱ አካል ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም ከንቲባዋ አረጋግጠዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በቀጣይ ቀናት በየምርጫ ክልላቸው በመውረድ ከመራጮች ጋር እንደሚወያዩም ተጠቁሟል።

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት

በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament

በዩቲዩብ https://www.youtube.com/watch?v=cp_8F5TEeFE

በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews

በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr

በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ