የኢኖቬሽን እና የቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በክዋኔ የኦዲት ግኝት መሰረት እያከናወነ ያለው ተግባር ሊሻሻል እንደሚገባ ተመላከተ

 (ዜና ፓርላማ) መጋቢት 17 ቀን ፣ 2017 ዓ.ም፤ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የፕሮጀክት ውል እና የሰው ሀብት አስተዳደር አፈፃፀም ውጤታማነትን በተመለከተ የ 2015/16 የተከናወነ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት መነሻ በማድረግ ይፋ የውይይት መድረክ አካሄዷል፡፡ 

የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ የሺእመቤት ደምሴ (ዶ/ር) እንዳሉት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፕሮጀክቶች አፈፃፀም ጋር ተያይዞ ዝቅተኛ አፈፃፀመም ማሳየቱን ጠቁመዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመንግስትም ይሁን በአጋር ድርጅቶች ድጋፍ ለሚሰራቸው ለእንዳንዱ ፕሮጀክቶች የዳሰሳና የአዋጭነት ጥናት አለመስራቱ በፕሮጀክቶች አፈፃፀም ለታዩ ክፍተቶች መፈጠር ምክንያት መሆኑን አብራርተዋል።

በቀጣይም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዳሰሳና የአዋጭነት ጥናት በመስራት ክፍተቶቹን ማረም እንደሚገባ እና ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡

አያይዘውም የፕሮጀክቶች መዘግየትና መጓተት ብሎም ቅድሚያ መሰጠት ያለባቸው ፕሮጀክቶችን ቅድሚያ የመስጠት ችግር መኖሩን ጠቁመው፣ በተያዘላቸው ጊዜ ያላለቁ ፕሮጀክቶች ወቅታዊ ሁኔታ የማይታወቅ ሲሆን፣ የፋይናንስና የፊዚካል አፈፃፀማቸው የተስማሚነት ችግር እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ፕሮጀክቶች ሳይጠናቀቁ አቋርጦ በጀቱን ወደ ሌላ ፕሮጀክት የማዘዋወር ሂደት ረገድ የህግ፣ የመመሪያ፣ የአሰራር ጥሰት የታየበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል ነው ያሉት፡፡

ከሰው ሀብት ጋር ተያይዞም መስሪያ ቤቱ ሰራተኞችን በሪኮመንዴሽን የሚቀጥርበት ሁኔታ ህግና ስርዓት ያልተከተለ በመሆኑ ሰራተኞችን አወዳድሮ ሊቀጥርና አሰራሩ ሊታረም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ከንብረት ማስመለስ ጋር በተያያዘም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የለቀቁና ጡረታ የወጡ ሰራተኞች ያልመለሷቸውን በጥቅል ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን የመንግስትና የህዝብ ሀብት በአግባቡ የማስመለስ ስራ መስራት አለበት ብለዋል፡፡

የፌደራል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው በኦዲት ሪፓርቱ ላይ የቀረበው ሪፓርት በተወሰኑ ፕሮጀክቶች ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቁመው፣ ተቋሙ አሁን የሚሰራቸው በርካታ ስራዎች መኖራቸውንና ከዚህ ተነስቶ አጠቃላይ ስራውን ሊፈትሽና ሊያሻሽል እንዲሁም ተጠያቂ የሆኑ አካላትን በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ተጠያቂ አድርጎ ሪፖርት ማድርግ ይገባልም ብለዋል፡፡

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተከበሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው ተቋሙ ለሀገር በርካታ ስራዎች እየሰራ መሆኑን አስታውሰው፣ ከፕሮጀክቶች፣ ከንብረት ማስመለስ፣ ካለ አግባብ ከተከፈሉ ክፍያዎች፣ ከሰራተኞች ቅጥር ጋር ተያይዞ በአፈፃፀም ሂደት ጉድለቶች መኖራቸውንና የእርምት እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ጠቁመዋል፡፡

አያይዘውም ወጪ ወጥቶ ያልተሰሩ ስራዎች ካሉ ፍተሻ እንደሚደረግም ነው ሚንስትሩ የተናገሩት፡፡ የፕሮጀክት ውል ሲያዝ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ማወቅና ማማከር ያለበት መሆኑ አዲስ መረጃ መሆኑንና በቀጣይ በአግባቡ የሚፈፀም መሆኑን ጠቁመው፣ በአጋር አካላት በተለይ በአለም ባንክ አማካኝነት የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ያሉንን ሀገራዊ ስትራቴጂዎችና ንድፎች መሰረት ተደርጎ እንደሚቀረፁ አስረድተዋል።

ስለዚህ የፕሮጀክቱ አዋጭነት፣ አስፈላጊነት፣ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑ በሀገራዊ ስትራቴጅ መሰረት ከባንኩ ጋር በመመካከር ተቀርፀው እንደሚሰሩም ነው ያብራሩት።

በተመሳሳይም አገር አቀፍ አንድምታ ያላቸውን ጉዳዮች ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ተነጋግረን ነው የምንፈርመው ያለ እርሱ ይሁንታ አንሰራም፤ የፍትህ ሚኒስቴር ይሁንታ የሚያስፈልጋቸው ከሆነም የፍትህ ሚኒስቴርን እናሳውቃለን ብለዋል ሚንስትሩ የተከበሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ።

 (በኃይለማርያም አየለ)