ምክር ቤቱ በመሠረተ-ልማት እና ኮንስትራክሽን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አማካይነት ከሕዝብ የጠመራቸውን ጥያቄዎች እንዲሁም ራሱ በመስክ ምልከታ የሰበሰባቸውን ጥያቄዎች አቅርቧል። እንደዚሁም የምክር ቤት አባላት በርካታ ጥያቄዎችን እና አስተያየቶችን ሰንዝረዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቀደም ሲል ከቋሚ ኮሚቴው ለተነሱት ጥያቄዎች እና ለተሰነዘሩት አስተያየቶች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥቷል። ከአባላት የተነሱትን ጥያቄዎች በተመለከተም፤ እንደ ሀገር ካለን ዓቅም፣ በሁሉም አካባቢዎች ለሚነሱት የመንገድ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ይከብዳል ብሏል። የክልሎችን ዓቅም በመገንባት፤ በፌዴራል መንግስት ብቻ የማይመለሱትን የመንገድ ግንባታዎች ለመመለስ ዕቅድ መያዙ ተገልጿል። የተቋራጮችን የፍትሐዊነት ችግር ለመፍታት የታሰበ መፍትሔ እንዳለም ተጠቁሟል።

ምንም እንኳን ከ90 እስከ 95 በመቶ የዘርፉ የግንባታ ጥሬ ዕቃዎች ሀገር ውስጥ የሚገኙ ቢሆንም፤ ያለቁት ምርቶች ከተለያዩ ሀገራት ማለትም ከስፔን፣ ከቻይና እና ከመሳሰሉት ሀገራት በቢሊየኖች በሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ ወጪ እንደሚገቡ፤ ሚኒስቴሩ አብራርቷል። ከነባሩ የግንባታ መንገድ በመውጣት፤ አዲስ እና የከተሜነትን (Urbanization) ቀጣይ ፍላጎት በሚመልስ መልኩ፤ አዲስ የግንባታ መንገድ መከተል እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።

መንገዶችን በተመለከተ፤ የአንዳንዶቹን ኮንትራት መንግስት በፀጥታ ችግር ማቋረጡን ሚኒስቴሩ ገልጿል። ባሌን እና አርሲን የሚያገናኙ መንገዶች በግንባታ ላይ መሆናቸውን እንደዚሁ አስረድቷል። አዲስ አበባ ጫንጮ የዋና መንገድ እየተከናወነ እንደሚገኝም ጠቁሟል።

"መንገድ ለመገንባት አሳማኝ ምጣኔ-ሀብታዊ እና ተያያዥ ምክኒያቶች ሊኖሩ ይገባል" - በምላሹ እንደተጠቆመው።

"የመሬት ባለይዞታዎች ቀርበው ይዞታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው፤ የካዳስተር መረጃ አያያዝ በሚፈለገው ደረጃ አልተያዘም። በአንጻሩ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራን ለማስቀረት ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ከመልካም አስተዳደር ጋር በተገናኘ፤ በየቦታው ችግር ያለባቸውን አመራር አካላት ከሕብረተሰቡ ጋር በመሆን ተጠያቂ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው" ከሪፖርት አቅራቢዎቹ እንደተመላከተው።

ክብርት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ፤ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ተስፋ ያለው ሴክተር ቢሆንም፤ ችግሩ ግን ዛሬ ተጀምሮ ዛሬ መፍትሔ የሚያገኝ ባለመሆኑ፣ የተከበረው ምክር ቤት እንዲያግዛቸው ጠይቀዋል። መንገድ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ታሳቢ ያደረገ እና የዜጎችን የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን ለማቃናት የሚዘረጋ ዓይነተኛ መሠረተ-ልማት መሆኑን፤ ሚኒስትሯ አስረድተዋል። ለግንባታ የሚውሉ ግብዓቶችን በተመለከተም፤ ከፌዴራል የማዕድን ሚኒስቴር ጋር በመሆን በሀገር ውስጥ ለማምረት መታቀዱንም፤ ሚኒስትሯ ጠቁመዋል። መንግስት በዓመት 4 መቶ ሺህ ቤቶችን እየገነባ ለዜጎች ለማስተላለፍ ዕቅድ ይዟል - ሚኒስትሯ እንዳስታወቁት።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመሠረተ-ልማት እና የኮንስትራክሽን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ስብሳቢ የተከበሩ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቀደም ሲል የተሰጡትን ግብረ-መልሶች ተቀብሎ፣ የዕቅድ አካል አድርጎ ውጤት ማምጣቱን በጥንካሬ አንስተዋል። በልዩ ሁኔታ በትኩረት መሠራት ያለበት፤ ከቤት ግንባታው አኳያ የ10 ወራት አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ስለሆነ፣ እንዲሻሻል ጠቁመዋል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የአሠራር እና የሕግ ማዕቀፍ ዘርግቶ እንዲሠራም፤ ሰብሳቢዋ አሳስበዋል።

በአጠቃላይ በከተማ እና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ከዕቅድ አኳያ ብዙ መሻሻሎች ቢኖሩም፤ ከተሞችን የብልጽግና ማዕከላት እና ለነዋሪዎቻቸው ምቹ ከማድረግ አንጻር ብዙ መሠራትእንዳለበት፤ ሰብሳቢዋ አሳስበዋል። በዚህም የዕለቱ 12ኛ መደበኛ ጉባዔ ተጠናቋል።