(ዜና ፓርላማ)፤ ሰኔ 29፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ዛሬ ባካሄዱት 6ኛው ልዩ ስብሰባ፤ በንጹሐን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጉዳት በተባበረ ድምፅ አወገዙ፡፡

በቀጣይ መሰል አደጋዎችን ለመከላከል በጋራ እንደሚቆሙ ያረጋገጡት አባላቱ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም ከጐናቸው በመቆም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዚህ ስብሰባው አያይዞም፤ በግፍ በተገደሉት ንጹሐን ዜጎች ጉዳይ ተወያይቶ የውሳኔ ሐሳብ አስተላልፏል።

የዕለቱን መርኃ-ግብር በግፍ ለተጨፈጨፉት ዜጎች የአንድ ደቂቃ የኅሊና ጸሎት በማድረግ የጀመረው ምክር ቤቱ፤ በሀገራችን በየትኛውም ክልል እና አካባቢ በሲቪል ዜጎች ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት ያስከተሉ እንዲሁም ንብረት ያወደሙ ግለሰቦች በሕግ እንዲጠየቁ ወስነዋል፡፡

ምክር ቤቱ የሕብረተሰቡን ሰላም እና ደኅንነት በማስጠበቅ ሂደት እስከ መሥዋዕትነት ድረስ ዋጋ የከፈሉ የመንግስት ባለስልጣናት እንዳሉ ሁሉ፤ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡት ደግሞ ተጠያቂ እንዲሆኑም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ አቶ ታገሠ ጫፎ በበኩላቸው በንጹሐን ዜጎች ላይ የተፈፀመው ድርጊት እንዳሳዘናቸው ገልፀው፤ ለአፍሪካ ሀገራት የነፃነት ተምሳሌት ሀገር የህዝቦችን አንድነት በማጠናከር ለብዙ ዘመናት የተዘራውን ጥላቻ ነቅለን አውጥተን ለቀጣዩ ትውልድ ሰላም የሰፈነባት ሀገር ለልጆቻችን ማስረከብ ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በጥላቻ ምትክ አብሮነትን፣ ወንድማማችነትን፣ ፈቅርን ኢትዮጵያዊነትን በመስበክ በዕኩይ ዓላማ ያላቸውን ሃይሎች ተልዕኮ ማክሸፍ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ተግባራዊ የሆነ እርምጃ በመውሰድ በየደረጃው ያለ አመራር ከፌዴራል እስከ ክልል የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ያልተወጡ አካላት ተጠያቂነት በማስፈን በሀገራችን ላይ ሰላምና ደህንነት እያረጋገጡ መሄድ እንደሚገባ የተከበሩ አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሠ ጫፎ ተናግረዋል፡፡

የተከበሩ አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሠ አክለውም፤ ሀገራችን ለማፍረስ የሚፈልጉ ሃይሎች የጠነሰሱት ሴራ ለማምከን ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአንድነት መቆም እንደሚጠበቅባቸው መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

የተከበሩ አፈ ጉባኤ አቶ ተገሰ ጫፎ በቀጣይ የሚቋቋመው ኮሚቴ ከሁሉም ክልሎች፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፤ ፆታን እና ሃይሞኖትን ስብጥርነት ያካተት እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡

የተከበሩ ምክትል አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው፤ ይህ ለውጥ እንዲመጣ ዋጋ ያልከፈለ ዜጋ የለም ይህን ለማደናቀፍ የሚጥሩ ኃይሎችን በጋራ ቆመን በጽናት መታገል ይኖርብናል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር የተከበሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው፤ የተፈጸመውን ድርጊት አውግዘው፤ መንግስት ከምንጊዜው በላይ የዜጎችን ሰላምንና ደህንነት ለማስጠበቅ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም መንግስት አስተዳደሩ እና በፀጥታ ሃይሉ መዋቅሩን በማጠናከር በርካታ ሥራዎች እየሰራ እንደሆነና መረጃ በተገኘባቸው አካላት አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ተናግረውል፡፡

የምክር ቤት አባላትም፤ የተፈጸመውን የዜጎችን ጭፍጨፋ አውግዘው፤ የመንግስት ዋና ተልዕኮው የዜጎችን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ በመሆኑ ሃላፊነታቸውን ያልተወጡ ከታች እስከ ላይ ያሉ አመራሮችን መፈተሽ እንዳለበት ጠይቀዋል፡፡

አክለውም የምክር ቤት አባላት ለቀጣይ እንደዚህ ያለ ድርጊት እንዳይፈጸም አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ከጥቃቱ ለተረፉ ዜጎች መንግስት አስፈላጊውን ጥበቃ እና ወቅቱም ክረምት በመሆኑ መሰረታዊ የሆኑ መጠለያ፣ ምግብ እና አልባሳትን ፈጥኖ እንዲያቀርብላቸው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ምክር ቤቱ በልዩ ጉባዔው የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ፤ ውሳኔ ቁጥር 10/2014 በአንድ ደምፀ ተአቅቦ እና ተቃውሞ፤ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡

በ መኩሪያ ፈንታ