የካፒታል ገበያ የተሻለ ለውጥ ማምጣት ይችላል ተባለ፤

(ዜና ፓርላማ) ሚያዚያ 06/2013 ዓ/ም፡- የገቢ፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በካፒታል ገበያ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት አዋጁ ከጸደቀ የተሻለ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ተገልጿል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ውይይቱን ያደረገው ከብሄራዊ ባንክ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ከተለያዩ ተቋማት ጋር ሲሆን፤ በረቂቅ አዋጁ ስለ ካፒታል ገበያ ምንነትና አስፈላጊነት ሰፊ ማብራሪ ተሰጥቷል፡፡

የብሄራዊ ባንክ የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ መለሰ ምናለ አዋጁን ለማርቀቅ ከአንድ ዓመት በላይ እንደፈጀ ጠቁመው፤ አዋጁ ከጸደቀ በኋላ ሰፊው ህዝብ እንዲገለገልበት የሚያስችል ግብዓት ለመሰብሰብ ያለመ ውይይት እንደሆነም  አስረድተዋል፡፡

ካፒታል ገበያ ዋና ዓላማው የረጅም ጊዜ የፋይናንስ ቆጣቢዎችንና ብድር ፈላጊዎችን የሚያገናኝ ገበያ እንደሆነ አማካሪው አስረድተው፤ በሀገራችን እንደዚህ አይነት ገበያ ባለመኖሩ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በባንክ ፋይናንስ ብቻ እንደተወሰነ በዝርዝር አስገንዝበዋል፡፡

ባንኮች የአጭር ጊዜ ቁጠባ ሰብስበው ለአጭር ጊዜ እንጂ ለረጅም ጊዜ ስለማያበድሩ የረጅም ጊዜ ቆጣቢዎች እንደ ማህበራዊ ዋስትና ድርጅት፣ መድህን ድርጅት እንዲሁም ግለሰቦች ለረጅም ጊዜ ጡረታ መቆጠብ ቢፈልጉ ፋይናንሳቸውን ኢንቨስት የሚያደርጉበት የገበያ መድረክ አለመኖሩንም የኢኮኖሚ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

አቶ መለሰ አያይዘውም የስራ እድል ፈጠራን የመሳሰሉ ጠቃሚ የሆኑ ፕሮጀክቶችን ፋይናስ ለማድረግ የሚፈልጉ አምራች ሀይሎች ፋይናንስ የሚያደርጉበት መድረክ ባለመኖሩ ፕሮጀክቶቹ በስራ ላይ ሲውሉ አይታዩም ብለዋል፡፡

የካፒታል ገበያ ተሞክሮ ከአሜሪካ፣ ከሲንጋፖር እና ከኩየት ልምድ እንደተቀሰመ አስረድተው ከባንኮች ማህበር እና ከኢንሹራንስ ሀላፊዎች ጋር ውይይት እንደተደረገም የብሄራዊ ባንኩ የኢኮኖሚ አማካሪ አስገንዝበዋል፡፡

የሴሉላር ኮንሳልቲንግ ንግድ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር አቡሽ አያሌው ኢትዮጵያ ወደ ካፒታል ገበያ መምጣቷ ኢኮኖሚው በተለያዩ ፋይናንሶች ታፍኖ የነበረ መሆኑን ጠቁመው፤ ያሁኑ አዋጅ ግን የተሻለ ለውጥ ያመጣል ብለዋል፡፡

አማካሪው የካፒታል ገበያን ለማቅረብ ስነ-ምህዳሮቹ መሟላት እንዳለባቸው አስገንዝበው መጀመሪያ ጠንካራ የሂሳብ አያያዝና ሪፖርት መቅረብ እንዳለበትም አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም የገቢ፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ያየሽ ተስፋሁነኝ ባለድርሻ አካላቱ ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽና የተለያዩ ግብዓቶችን በመስጠታቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በ መስፍን አለሰው