(ዜና ፓርላማ)፤ መስከረም 13፣ 2015 ዓ.ም፤ የኮከስ አደረጃጆችን አጠናክሮ የሴቶችን እኩል ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ለተጀመረው የሀገር ግንባታ ወሳኝ ሚና እንዳለው የ6ኛው ዙር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴት ተመራጭ ኮከስ አባላት ገልጸዋል፡፡

የኮከሱ አመራሮች ይንን የገለጹት፤ በትላንትናው እለት በአዋሽ ከተማ አስተዳደር የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ሴት የምክር ቤት አባላት የሴቶች ኮከስ የምስረታ ጉባዔ በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡

በኮከሱ የምስረታ ጉባዔም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና የኮከሱ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የ11 ክልሎች አፈ-ጉባዔዎች ተሳትፈዋል፡፡

በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የሴት ኮከስ ሰብሳቢ የተከበሩ ወይዘሮ ኪሚያ ጁንዲ የምስረታ ጉባዔውን መርሐ ግብር በይፋ በከፈቱበት ወቅት የኢትዮጵያ ሴቶች በፅኑ ታግለው ባገኙት ድል ለመብቶቻቸው ከለላ የሆነውን ሕገ-መንግስት ከህዝብ ጋር በመሆን አጽድቀው በተግባር ማዋል እንደቻሉ አስገንዝበዋል፡፡

ሴቶች ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንዲሁም በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው የመከበር፣ እኩል ተሳታፊና ፍትህዊ ተጠቃሚ መሆናቸውን የማረጋገጥ ጅማሮዎች እየታዩ መሆኑን ሰብሳቢዋ ኪሚያ ጁንዲ አስታውሰዋል፡፡

የተመራጭ ሴቶች ኮከስ አባላት የመሪነት ሚና መጫዎት እንዳለባቸው እና በምክር ቤቶችም በሕግ ማውጣት፣ በክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም በሕዝብ ውክልና ሥራዎች የላቀ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ ወይዘሮ ኪሚያ አሳስበዋል፡፡

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አስያ ከማል በበኩላቸው፤ ቀደም ባሉ ጊዜያት በክልሉ የሴቶች ተሳትፎ ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ የሴቶች ኮከስ አደረጃጃት ሊመሰረት አለመቻሉን አስታውሰው፤ አሁን ላይ በሁሉም ዘርፍ የሴቶች ተሳትፎ እየጨመረ በመምጣጡ ምክንያት የኮከስ አደረጃጀት መመስረት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

የኮከስ አደረጃጀት መመስረቱ ሴቶት ወደ አመራርነት እንዲመጡ፣ የውሳኔ ሰጭነት አቅማቸው እንዲጎለብት እና ፍትህዊ ተጠዋሚነታቸውን ለማረጋገጥ ያግዛል ያሉት አፈ-ጉባዔ አስያ ከማል፤ የክልሉ አርብቶ አደር የማህበረስብ ክፍሎች ወደ እርሻ ሥራ እና ከተሜነት ተቀይረው ኑሮአቸው እንዲሻሻል የላቀ ጠቀሜታ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

የአፋር ክልል ምክር ቤት አባል እና የኮከስ ስራ አመራር ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ነስሮ ኡዳ በበኩላቸው፤ የኮከስ አደረጃጀት መመስረቱ በትምህርት፣ በጤና፣ በኢኮኖሚ እና በፖለቲካ ወደ ኋላ የቀሩ አርብቶ አደር የማህበረሰብ ክፍሎችን ህይወት ለማሻሻል ጠቀሜታው የላቀ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የሴቶችን አቅም ለመገንባት እና የፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ ይህ የኮከስ መመስረት ፋይዳው የጎላ እንደሆነ የገለጹት ወይዘሮ ነስሮ፤ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ዘርፈ-ብዙ ችግሮችን እልባት ለመስጠት በኮከስ ምስረታው ኃላፊነት የተሰጣቸው ሴቶች ከሕዝቡ ጋር በትብብር መስራት የሚጠበቅባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በ ተስፋሁን ዋልተንጉስ

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት

በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament

በዩቲዩብ https://www.youtube.com/watch?v=cp_8F5TEeFE

በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews

በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr

በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ