(ዜና ፓርላማ)፣ ሰኔ 30፣ 2015 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የ2015 በጀት ዓመት የምክር ቤቱ የስራ ዘመን የተሳካ እንደነበር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ወይዘሮ ሎሚ በዶ ገልጸዋል፡፡

ምክትል አፈ-ጉባዔዋ ይህንን የገለጹት የምክር ቤቱን የ2015 በጀት ዓመት ማጠቃለያ ሪፖርት ለምክር ቤት አባላት ባቀረቡበት ወቅት ነው፡፡

ምክር ቤቱ ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ፤ በሕግ አወጣጥ፣ በክትትል እና ቁጥጥር፣ በሕዝብ ውክልና፣ በፓርላማ ዲፕሎማሲ እና በአቅም ግንባታ በኩል ስኬታማ ስራዎችን መከወን መቻሉን ነው የተከበሩ ወይዘሮ ሎሚ ያብራሩት፡፡

ሕግ አወጣጥን በተመለከተ በበጀት ዓመቱ ለምክር ቤቱ ሃያ አምስት ረቂቅ አዋጆች እና አምስት ረቂቅ ደንቦች እንዲጸድቁ ቀርበው ሃያ ረቂቅ አዋጆች እና አንድ ደንብ በዝርዝር እና በተናጠል ምርመራ ተደርጎባቸው መጽደቃቸውን ምክትል አፈ-ጉባዔዋ ገልጸው፤ ከጸደቁት አዋጆች ውስጥ አስራ አምስት አዋጆች በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ስራ ላይ እንዲውሉ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

የጸደቁት አዋጆች በይዘታቸው የአርሶ-አደሩን ተጠቃሚነት የሚያሻሽሉ፣ የከፍተኛ ትምህርት ዘርፉን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማረጋገጥ እና ሀገራዊ ፋይዳውን ከፍ ለማድረግ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ትስስርን በማጠናከር ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ለማልማት ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ምክትል አፈ-ጉባዔዋ አብራርተዋል፡፡

ምክር ቤቱ በክትትል እና ቁጥጥር ተግባራት የአስፈጻሚ ተቋማትን ዕቅድና አፈጻጸሞች በምን ደረጃ ላይ እንዳሉ በበጀት ዓመቱ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች 326 ልዩ ልዩ የመስክ ምልከታዎችን ማካሄድ መቻሉን የተከበሩ ወ/ሮ ሎሚ አስታውቀዋል፡፡

በተደረጉት የመስክ ምልከታዎች፤ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም፣ የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች መከበራቸውን፣ የተቋማት የተግባራት አፈጻጸም እና የኦዲት ግኝቶች ላይ የተወሰዱ እርምጃዎች እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚያስችል ከትትል በማድረግ በአንዳንድ አስፈጻሚ ተቋማት የታዩ ችግሮች በፍጥነት እንዲፈቱ እና የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ መደረጉን የተከበሩ ወ/ሮ ሎሚ አስረድተዋል፡፡

የሕዝብ ውክልና ተግባራትን በተመለከተ ምክር ቤቱ ኃለፊነትን ከተጠያቂነት ጋር ለማረጋገጥ ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች እና አሰተያየቶች በመለየት እና በማደራጀት ምላሽ የሚሹ የሕዝብ ጥያቄዎች በየደረጃው ከሚገኙ አስፈጻሚ አካላት ጋር ምክክር እንደተደረገባቸው ምክትል አፈ-ጉባዔዋ ጠቅሰዋል፡፡

እንዲሁም በበጀት ዓመቱ ምክር ቤቱ ከሌሎች ሀገራት ጋር ልምድ ለመለዋወጥ፣ ወዳጅነትን ለማጠናከር፣ የሀገርን እና የምክር ቤቱን ገጽታ ለመገንባት የሚያግዝ የፓርላማ ዲፕሎማሲ በአውሮፓ እና አፍሪካ ሀገራት ማከናወን መቻሉንም ወይዘሮ ሎሚ አብራርተው፤ የፓርላማ ዲፕሎማሲ ወዳጅነት ቡድኖች ሁሉንም ሀገራት ባቀፈ ሁኔታ መቋቋሙን ገልጸዋል፡፡ 

በሌላ በኩል ለአንዳንድ አዋጆች ደንብ እና መመሪያ በተገቢው ጊዜ አለመውጣቱ ለአፈጻጸም አስቸጋሪ መሆኑን፣ ለቋሚ ኮሚቴዎች የተመሩ አዋጆች በአባላት አሠራር እና ሥነ-ምግባር ደንብ ከሚፈቅደው ጊዜ በላይ የማዘግየት ሁኔታ መኖሩ እና በፌደራል ዋና ኦዲተር የኦዲት ግኝቶች ሪፖርት መሰረት በአስፈጻሚ አካላት ላይ ተገቢ የሆኑ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ማድረግ ላይ በሚፈለገው ልክ ማከናወን አለመቻሉን የተከበሩ ወ/ሮ ሎሚ በእጥረት አንስተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የታዩ ክፍተቶችን በቀጣዩ ዓመት በማረም ምክር ቤቱ ሕገ-መንግስታዊ ተልዕኮውን እንደሚወጣ ምክትል አፈ-ጉባዔዋ ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም 6ኛው ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2ኛ ዓመት የስራ ዘመኑን በዛሬ ዕለት ማጠናቀቁን የተከበሩ አፈ-ጉባዔ ታገሠ ጫፎ አስታውቀዋል፡፡

በ ስሜነው ሲፋረድ

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት፡- 
በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament 
በዩቲዩብ https://www.youtube.com/@FDREHOPR 
በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews 
በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr 
በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ