(ዜና ፓርላማ)፣ ነሐሴ 01፣ 2014 ዓ.ም.፤ ቢሾፍቱ፤ የፌዴራል፣ የክልሎች እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ጽሕፈት ቤቶች የስራ ኃላፊዎች እና ተወካዮች የጋራ ምክክር ፎረም የአሠራር መምሪያውን አጽድቀዋል፡፡

የጋራ ምክክር ፎረም የአሠራር መምሪያውን ዓላማ እና ተግባራት በተመለከተ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የሕግ ጉዳዮች ጥናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም ውበት ገለጻ አቅርበዋል፡፡

የአሠራር መምሪያው፣ በሕግ አወጣጥ፣ በክትትል እና ቁጥጥር፣ በሕዝብ ውክልና እና በሙያዊ እና አስተዳደራዊ አገልግሎቶች የተሻሉ ምክክሮችን፣ በለውጥ ስራዎች አተገባበር፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና በሕዝብ ተሳትፎ የልምድ ልውውጦችን እና ተሞክሮዎችን በማስፋት ጠንካራ የምክር ቤት ጽሕፈት ቤቶችን ለመፍጠር ያለመ የአሠራር መምሪያ መሆኑን አቶ ኤፍሬም ገልጸዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት፣ የክልሎች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤቶች እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ጽሕፈት ቤቶች የፎረሙ አባላት መሆናቸውን አቶ ኤፍሬም አስረድተዋል፡፡

በመምሪያው ላይ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ፣ የክልሎች እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ጽሕፈት ቤቶች የስራ ኃላፊዎች እና ተወካዮች በጥልቀት ከተወያዩበት በኋላ መምሪያውን በሙሉ ድምጽ አጽድቀዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ፀሐፊ ዶክተር ምሥራቅ መኮንን በበኩላቸው፤ መድረኩ፣ ምክር ቤቶች ጠንካራ ሆነው ተልዕኳቸውን እንዲወጡ የሚያስችል የልምድ ልውውጦች የተገኙበት፤ አንዳንድ ክልሎች በጦርነት ውስጥ ሆነው በነበረበት ወቅት ጽሕፈት ቤቶቻቸው ለምክር ቤቶቻቸው ሲሰጡት የነበረው ሙያዊ እና አስተዳደራዊ አገልግሎት የሚደነቅ እንደነበር፣ በጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች እና ተወካዮች በኩል የቀረበውን ሪፖርት መሰረት አድርገው ገልጸዋል፡፡

ጽሕፈት ቤቶቹ በ 2014 ዓ.ም. የነበሩ ውስንነቶችን በመፍታት በ 2015 ዓ.ም. ለምክር ቤቶቻቸው የተሻሉ አሠራሮቸን ተጠቅመው የሚሰጡትን ሙያዊ እና አስተዳደራዊ አገልግሎት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ዶክተር ምሥራቅ አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ስሜነው ሲፋረድ

ቀን፡- ነሐሴ 01፣ 2014 ዓ.ም