(ዜና ፓርላማ)፤ ጥቅምት 6፣ 2015 ዓ.ም፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተከበሩ አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን የኢትዮጵያን እድገት እና ብልጽግና እውን ማድረግ እንደሚቻል አስገነዘቡ።

አፈ-ጉባዔው ይህንን የገለጹት ጅማ በተካሄደው የህግ አውጪዎች የጋራ መድረክ ማጠናቀቂያ በሸቤ ሱምቦ ወረዳ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው ያለሙትን የሩዝ ሰብል በጎበኙበት ወቅት ነው።

ይህን የሩዝ ሰብል የማልማት ጅማሮ በሁሉም ክልሎች ተሞክሮው መስፋት እንዳለበት ያመላከቱት አፈ-ጉባዔ ታገሰ፤ በአካል ተገኝተን የጎበኘነው ይህ የሩዝ ሰብል ወደ ኢንዱስትሪ ለምናደርገው ሽግግር ትልቅ አቅም የተገኘበት ተሞክሮ ነው ብለዋል።

የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው እንደሀገር የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

ስንዴን የማልማት ስራው በተለይ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በአፋር እና በሶማሌ ክልሎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶበት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ በዘርፉ ኦሮሚያ ክልል ግንባር ቀደም በመሆኑ ሌሎች ክልሎች ልምድ ሊቀስሙ እንደሚገባ አመላክተዋል።

በሸቤ ሱምቦ ወረዳ ወጣቶች በግብርናው ዘርፍ ህይወታቸውን ለመቀየር ተደራጅተው የሩዝ ሰብል ማልማተቸው የሚደነቅና የሚበረታታ ተግባር እንደሆነም አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ገልጸዋል።

ስንዴ ከውጭ ሀገራት ከማስገባት ይልቅ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሀገር የምትልክበት ደረጃ ላይ መድረሷ፤ በተለይም የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ የተጀመሩ የግብርና ልማቶች ተስፋ ሰጪ እንደሆኑ የተከበሩ አቶ አገኘሁ አስገንዝበዋል።

በጅማ ዞን የሸቤ ሱምቦ ወረዳ ግብርና ኃላፊ አቶ ነዚብ አብደላ፤ የጎጀብ ኪሼ አግሮ ኢንዱስትሪ ኃለፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከ250 በላይ ወጣቶች ያሉት ሲሆን በዘንድሮው የመኸር ወቅት 3500 ሄክታር የሩዝ ሰብል ማልማት እንደቻሉ አስረድተዋል።

በ ተስፋሁን ዋልተንጉስ

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት

በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament

በዩቲዩብ https://www.youtube.com/watch?v=cp_8F5TEeFE

በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews

በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr

በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ