(ዜና ፓርላማ)፣ ሐምሌ 30፣ 2014 ዓ.ም.፤ ቢሾፍቱ፤ የፌዴራል፣ የክልሎች እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች ጽሕፈት ቤቶች የጋራ መድረክ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አዘጋጅነት በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

መድረኩን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ፀሐፊ ዶክተር ምሥራቅ መኮንን የከፈቱት ሲሆን፣ የመድረኩን ዓላማም አስተዋውቀዋል፡፡

የመድረኩ ዓላማ፤ ለምክር ቤት አባላት እና አካላት የተደራጁ መረጃዎችን በማቅረብ ቀልጣፋ፣ ውጤታማ ሙያዊ ድጋፍ እና አስተዳደራዊ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችል የጋራ የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት መድረክ መሆኑን ዶክተር ምሥራቅ አብራርተዋል፡፡

የጋራ የምክክር መድረኩ የፌዴራል፣ የክልል እና የከተማ አስተዳደር ጠንካራ ምክር ቤት እንዲኖራቸው ለማስቻል፣ የምክር ቤት ጽሕፈት ቤቶች ቋሚ የግንኙነት ጊዜ በመፍጠር በተለያዩ ጉዳዮች ልምድ፣ ተሞክሮ፣ እና የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ ሚናው የጎላ መሆኑን የምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የአስተዳደራዊ ዘርፍ ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ ታምር ከበደ አስረድተዋል፡፡

አቶ ታምር አክለውም፤ የጋራ መድረኩ ጽሕፈት ቤቶች ለምክር ቤት አባላት እና አካላት፤ በሕግ አወጣጥ፣ በክትትል እና ቁጥጥር፣ በሕዝብ ውክልና እና ተያያዥ ተግባራት የሚሰጡትን ሙያዊ እና አስተዳደራዊ አገልግሎት በሚመለከት ልምድ እና ተሞክሮ የሚለዋወጡበት መድረክ ነው ብለዋል፡፡

የምክር ቤቱን ዕለት ተዕለት ሥራዎች ለሕዝቡ ተደራሽ ለማድረግ እና የተሻሉ አሠራሮችን በመዘርጋት ወደ ሕዝቡ ለመቅረብ በርካታ የለውጥ ሥራዎች መሰራታቸውን የገለጹት ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የሙያዊ ድጋፍ ዘርፍ ምክትል ዋና ጸሐፊ ሄኖክ ስዩም (ዶክተር) ናቸው፡፡

ዶክተሩ አክለውም፤ ምክር ቤቶች ተልዕኳቸውን በብቃት እንዲወጡ መሰል መድረኮች የማይተካ ሚና እንዳለቸው ገልጸዋል፡፡

የክልሎች እና የከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ጽሕፈት ቤቶች የስራ ኃላፊዎች እና ተወካዮች፤ ለምክር ቤቶቻቸው የሚሰጡትን ሁለንተናዊ አገልግሎት ለማቀላጠፍ እና ምክር ቤቶች የተቋቋሙለትን ዓላማ እንዲወጡ ለማስቻል፤ በፌዴራሉ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት በኩል በተለይም፤ በቴክኖሎጂ፣ ቤተ-መጽሐፍትን በማዘመን እና በሚዲያ አጠቃቀም በኩል የተሰሩ የለውጥ ስራዎችን በተሞክሮነት በመውሰድ የሚሰጡትን አገልግሎት የበለጠ ለሕዝብ ተደራሽ ማድረግ እንደሚችሉ ዶክተር ሄኖክ አብራርተዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ፣ የክልሎች እና ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች እና ተወካዮች የየምክር ቤቶቻቸውን ስራዎች ወደ ሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ ያከናወኗቸውን የለውጥ ስራዎች እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡

የጋራ ምክክር መድረኩ በነገው ዕለትም ቀጥሎ እንደሚውል ከውይይት መርሃ-ግብሩ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ዘጋቢ፡- ስሜነው ሲፋረድ

ቀን፡- ሐምሌ 30፣ 2014 ዓ.ም