የፖለቲካ ፓርቲዎች አስተዳደርና የምርጫ ሥነምግባር ረቂቅ አዋጅ ለቋሚ ኮሚቴው ተመራ

 (ዜና ፓርላማ) ሰኔ 27 2017 .ም፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 4 ዓመት የስራ ዘመን 2 ልዩ ስብሰባው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ በዝርዝር ለሚመለከተው የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ በረቂቅ አዋጁ ላይ የተዘጋጀውን አጭር ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡

ቀደም ሲል የነበረውን አዋጅ ተከትሎ ቦርዱ ያስፈጸመው ጠቅላላ ምርጫ በህግ ከፍተት ምክንያት የተስተዋሉ ችግሮችን እንዲሁም በፖለቲካ ፓርቲ አስተዳደር ስራዎች ላይ ያሉ የህግ ክፍተቶችን ለማረም የተዘጋጀ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ እንደሆነ አፈ ጉባኤው አስረድተዋል፡፡

የማሻሻያ አዋጁ የምርጫ ተሳታፊ ባለድርሻ አካላት ምርጫውን ሰላማዊ እና ፍትሀዊ በማድረግ ከማስፈጸም አንጻር ያላቸውን መብትና ግዴታ ለመደንገግ የወጣ ስለመሆኑም የተከበሩ አቶ ታገሰ ጠቁመዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ ወጥነት፣ ግልጽነት እና ከህገመንግስታዊ መርሆች እና አለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎች ጋር በማጣጣም ነባሩን ህግ በማሻሻል እንደሚያጠናክርም ገልጸዋል።

ማሻሻያው ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ሌሎች የተገለሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በምርጫ እና በፖለቲካ የተሻለ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ያስችላልም ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ነጻነትና የአሰራር ቅልጥፍና ለማሳደግ፣ ሰፊ የፖለቲካ ተሳትፎና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችል ማሻሻያ አዋጅ እንደሆነም የተከበሩ አቶ ታገሰ ባቀረቡት ማብራሪያ ገልጸዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ የተመራለት ቋሚ ኮሚቴ በጥልቀት ሊያየው ይገባል ያሏቸውን ሀሳቦች አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም ምክር ቤቱ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 24/2017 አድርጎ ለዝርዝር እይታ ለዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መርቷል።