(ዜና ፓርላማ)፤ ነሐሴ 04፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የፓን አፍሪካ ፓርላማ ምክትል ፕሬዚዳንት የተከበሩ ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ፤ ከዩጋንዳ ከመጡ የፓን አፍሪካ የፓርላማ አባላት ጋር በዛሬው ዕለት ተወያዩ፡፡

ምክትል ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካ ፓርላማ የምክትል ፕሬዚዳንትነት ስፍራ መያዟን ገልጸው፤ ዩጋንዳ ቀጣዩን አህጉራዊ ጉባዔ ለማስተናገድ ኢትዮጵያን ማስፈቀድ፣ ማነጋገር እና ማሳመን ስላለባት አባላቱ መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡

የተከበሩ ዶክተር አሸብር ለጊዜው ለፓን አፍሪካ ፓርላማ የተዘጋጀ ቢሮ እና ቁሳቁስ እንደሌለ አስረድተው፤ በቀጣይ ቢሮ እና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችን በተፋጠነ ሁኔታ ለማሟላት ከኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቃል እንደተገባላቸው ተናግረዋል፡፡

የተከበሩ ዶክተር አሸብር ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካ ፓርላማ ምክትል ከመሆኗ አንጻር ኃላፊነቷን በአግባቡ ለመወጣት ፍጹም ቁርጠኛ ናት ካሉ በኋላ፤ ስለ ምሥራቅ አፍሪካ እና ስለ አፍሪካ ችግሮች ከልዑካን ቡድኑ አባላት ጋር መነጋራቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዩጋንዳ የመጡት የፓን አፍሪካ የፓርላማ ልዑካን በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የምታካሂደውን የታላቁን የኅዳሴ ግድብ በተመለከተ የምታራምደውን አቋም እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል የፓን አፍሪካ ፓርላማ ቢሮ ለማቋቋም በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

የተከበሩ ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ፤ ቀደም ሲል ሀገራቸውን እና የምሥራቅ አፍሪካን ወክለው ለሁለት ያህል ጊዜያት በምክትል ፕሬዚዳንትነት ማገልገላቸው ይታወቃል፡፡ በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ ሚድራንድ በተካሄደው አህጉራዊው ስብሰባም፤ በተመሳሳይ ሁኔታ በከፍተኛ ድምጽ በምክትል ፕሬዚዳንትነት መመረጣቸው ይታወሳል፡፡

ዘጋቢ፡- መስፍን አለሰው

ቀን፡- ነሐሴ 04፣ 2014 ዓ.ም