(ዜና ፓርላማ)፤ ሰኔ 26፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዳማ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት፤ በ2013/14 የበጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ረገድ፣ አመራሩን እና ሠራተኛውን ዛሬ አወያየ።

በአዳማ ከተማ በተካሄደው በዚህ ውይይት የጽሕፈት ቤቱ ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ምሥራቅ መኮንን፤ የተቋሙ አጠቃላይ አፈጻጸም በፊት ከነበረው የተሻለ መሆኑን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ አሁንም ከተለመደው አሠራር መውጣት እና የባሕርይ ለውጥ ማምጣት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ ለየተሻለ ውጤት መትጋት አለብን ብለዋል።

ለዚህም ሲባል ሁሉም የሥራ ክፍል ኃላፊዎች በሥራቸው ካሉ ሠራተኞች ጋር በሥራ ዙሪያ መነጋገር እና መወያየት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

"ሁሌም በቅንነት ለመማር ዝግጁ በመሆን፣ ያለንን ዕውቀት በመተግበር፣ የምንመኘውን ለውጥ ለማምጣት የየራሳችንን አስተዋጽዖ ማድረግ አለብን። ለሠራተኞች የሚሰጡት የዓቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎችም ችግር ፈቺ እና ውጤታማ እንዲሆኑ መሥራት ያስፈልጋል። አጠቃላይ አሠራርን የሚመለከት ስትራቴጂም ይዘጋጃል" ዶ/ር ምሥራቅ እንደተናገሩት።

የጽሕፈት ቤቱ አስተዳደራዊ ድጋፍ ዘርፍ ምክትል ዋና ፀሐፊ አቶ ታምር ከበደ በበኩላቸው፤ ሠራተኛው እየሰጠ ያለው አገልግሎት እየተሻሻለ መሆኑን ገልጸዋል። የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ደግሞ በየጊዜው በጥናት የተደገፉ ሙያዊ የዓቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በውጪ እና በውስጥ ዓቅም በመስጠት፤ የላቀ አገልግሎት መስጠት ይቻላል ብለዋል።

የጽሕፈት ቤቱን የማስፋፊያ ግንባታ በሚመለከትም እስከ መስከረም 30፣ 2015 ዓ.ም. ለማጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞ ተገቢው ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የጽሕፈት ቤቱ የሙያዊ ድጋፍ ዘርፍ ምክትል ዋና ፀሐፊ ሄኖክ ስዩም (ዶ/ር)፤ እንደ አጠቃላይ የተሻለ አፈጻጸም ቢስተዋልም፣ የሚፈለገውን ርካታ ያስገኘ እና ደረጃውን የጠበቀ ነው ለማለት የማያስደፍር መሆኑን አሰረድተዋል። በቀጣይም አሠራርን በማዘመን፣ ምቹ ምኅዳር በመፍጠር፣ ያለንን ዕምቅ ዓቅም በማውጣት ውጤታማ ሥራ መሥራት አለብን ብለዋል።

"ተግተው የሚሠሩትን የማመስገን እና የማበረታታት እንዲሁም በአግባቡ የማይሠሩትን ተጠያቂ የማድረግ ባሕል ሊኖር ይገባል። እያንዳንዱ የሥራ ክፍልም የተሻለ ሥራ ለመሥራት በደንብ መዘጋጀት አለበት። ከዚህ ጋር ተያይዞም የጽሕፈት ቤቱ አዲስ አደረጃጀት በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ውስጥ ይተገበራል" እርሳቸው እንዳሉት።

ከጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞች፤ "ከኑሮ ውድነት አኳያ የደመወዝ እና የጥቅማ-ጥቅም ማሻሻያ ቢደረግ፣ ሠራተኛው በየጊዜው ከአመራሩ ጋር የሚወያይበት መድረክ ቢኖር፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነት ያለው አሠራር ቢፈጠር እና የመኖሪያ ቤት ችግር የሚፈታበት ሁኔታ ቢመቻች" የሚሉ አስተያየቶች እና ሌሎች ጥያቄዎች ተነስተዋል። ለእነዚህ እና በውይይቱ ለተነሱት ተጨማሪ ጥያቄዎች፤ በየደረጃው ያሉት የጽሕፈት ቤቱ አመራሮች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በ ፋንታዬ ጌታቸው