(ዜና ፓርላማ)፤ ሰኔ 15፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሥራዎች አማካሪ ኮሚቴ የጽ/ቤቱን የተግባር አፈፃፀም ከጽ/ቤቱ የማኔጅመንት አባላት ጋር ገምግሟል፡፡

በጽ/ቤቱ የሥራ ሃላፊዎች የአንድ ወር ተኩል የተግባር አፈፃፀም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ሰፊ ውይይትም ተደርጎበታል፡፡

በውይይቱ የኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ መለሰ መና የጽ/ቤቱ አሠራር ቀደም ሲል ከነበረው በእጅጉ መሻሻሎች እየታዩበት መሆኑን ገልፀው፤ ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል ግን ጽህፈት ቤቱ ስራዎችን ተጠያቂነት ባለው መልኩ ቆጥሮ በመስጠትና በመቀበል በቡድን መንፈስ ተናቦ መስራት እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡

በም/ቤቱ ቅጥር ግቢ እየተገነባ ያለው የማስፋፊያ ህንጻ ግንባታ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለቀጣዩ የስራ ዘመን ለስራ ምቹ እንዲሆን መሰራት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የኮሚቴው አባል የሆኑት የተከበሩ አቶ ከማል ሀሺ በበኩላቸው ጽ/ቤቱ የቡድን ስሜት ፈጥሮ ለምክር ቤቱ ተገቢውንና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ለጽ/ቤቱ አመራሮችም ሆነ ለሠራተኞች የቡድን ሥራን በተመለከተ ሣይንሣዊ በሆነ መንገድ ስልጠና ሊሰጥ እንደሚገባ ጠቁመው፤ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታትም የመወያየትና የመነጋገር ባህልን ማዳበር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሚዲያና ኮሚኒኬሽን የስራ ክፍሎች የነበረባቸውን ውስንነቶች በመቅረፍ ባከናወኑት ተግባር ለህብረተሰቡና ለሚዲያ ተቋማት ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ በመሆን ለውጥ ከታየባቸው የሥራ ክፍሎች ተጠቃሽ መሆናቸውንም አቶ ከማል ገልፀዋል፡፡

ምክር ቤቱን የሚያግዙ የጥናትና ምርምር ስራዎችም ተጠናክረው መቀጠልና ጥሩ ግብአት ይዘው መምጣት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል፡፡

የአማካሪ ኮሚቴው አባል የሆኑት ዶ/ር አብረሃም በርታ ጽ/ቤቱ ቀደም ሲል ከነበረው ሁኔታ አሁን ላይ የተሻለ መነቃቃት የታየበት መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይም በአመራሩና በሠራተኛው ዘንድ የሚስተዋሉትን የመናበብ ችግር ለመፍታት የችግሮቹን መንስኤዎች ለይቶ በትኩረት መስራት አለበት ብለዋል፡፡

ሀገርን መውደድ የሚለካው ስራን ከመስራት ባለፈ ከሥራው በሚገኘው ውጤት በመሆኑ ሁሉም በተሠማራበት የሥራ መስክ ሃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ከውይይቱ ተሣታፊዎች የተለያዩ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ተሰንዝረዋል፤ ለአብነት በየደረጃው የሚቀርቡ ጥያቄዎች ፈጣንና ተገቢ ምላሽ አለማግኘት፣ ምቹ የሆነ የስራ ቦታ አለመኖር፣ በ አይቲ፣ በግዥና ፋይናንስ እንዲሁም በሚዲያ የሥራ ክፍሎች የሚስተዋለው የሰው ሃይል እጥረት፣ የህፃናት ማቆያ እና ክሊኒክ የሚሠጡት አገልግሎት ከደረጃ በታች መሆኑ እና የመንግስትን አሠራር ተከትሎ ጥሩ የሰሩ ሰራተኞችን የማበረታታት እንዲሁም ጉድለት የታየባቸውን ተጠያቂ የማድረግ ስርአት አለመኖር የሚሉት ይገኙበታል፡፡

የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ዋና ፀሐፊና የሙያዊ ድጋፍ ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ሄኖክ ስዩም እና ምክትል ዋና ፀሐፊና የአስተዳደራዊ ድጋፍ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታምር ከበደ ከቤቱ ለተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ የተሰጡ ግበረ-መልሶችን ለቀጣይ ሥራ እንደ ግብዓት በመውሰድ እንደሚሰራባቸው ተናግረዋል፡፡

በ ፋንታዬ ጌታቸው