(ዜና ፓርላማ)፤ ሐምሌ 6፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ በሀገር ደረጃ ለሕዝብ መሠረታዊ አገልግሎት የሚያበረክቱ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ በቀጣይ መከተል ያለባቸውን አቅጣጫ አመላከተ።

ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን፣ ከኢትዮጵያ ቴሌኮሚዩኒኬሽን እና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ባካሄደው ውይይት፤ የተቋማቱን አገልግሎት በተመለከተ ከሕዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች ተቋማቱ በምን ደረጃ ምላሽ እየሰጡ እንደሆነ ገምግሞ አቅጣጫዎችን አመላክቷል።

ምክር ቤቱ የእነዚህን ተቋማት ሪፖርት ያዳመጠው እና ውይይት ያካሄደው፤ የምክር ቤቱ አባላት ቀደም ሲል በ2014 በጀት ዓመት መጋቢት ወር ወደተመረጡበት አካባቢ ተንቀሳቅሰው በሰበሰቡት የሕዝብ ጥያቄዎች ተመሥርቶ ነው።

አባላቱ ቁልፍ ምክር ቤታዊ ተግባር በሆነው የሕዝብ ውክልና ሥራ አማካይነት፤ የመረጣቸውን ሕዝብ ወርደው አወያይተዋል። በዚሁ ወቅትም ሕዝቡ ሰላም እና ፀጥታን፣ የኑሮ ውድነትን እና የዋጋ ግሽበትን፣ የመልካም አስተዳደርን፣ የልማት ፕሮጄክቶችን አፈጻጸም እንዲሁም በግጭቶች የወደሙ መሠረተ-ልማቶችን በተመለከተ፤ ጥያቄዎችን ማንሳቱን አስታውሰዋል፡፡

ምንም እንኳን በሪፖርት አቅራቢ ተቋማት በኩል አበረታች ውጤቶች እንዳሉ ምክር ቤቱ ቢያረጋግጥም፤ እነዚህን የሕዝብ አንገብጋቢ ጉዳዮችን በተመለከተ ጠንከር ያሉ ጥያቄዎችን ለተቋማቱ አንስቷል። በቀጣይ በየደረጃው የሕዝብን የልማት ፍላጎት ተመርኩዞ የማስተካከያ ርምጃዎች እንዲወሰዱም ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ታገሠ ጫፎ፤ የሕዝብ ውክልና ሥራው በዞን፣ በክልል እና በፌዴራል ደረጃ የሚፈቱ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለይቶ፤ በየደረጃው ለመፍታት ያላሳለሰ ጥረት መደረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ የውክልና ሥራውን ለማሳለጥ የሚያግዝ ቴክኖሎጂ መልማት እንዳለበትም አፈ-ጉባዔው ጠቁመዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች በሕዝብ ውክልና ሥራቸው ስለአካባቢያቸው ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነትን ማዕከል ያደረገ ሥራ ማከናወን እንደሚጠበቅባቸውም አፈ-ጉባዔ ታገሠ ጫፎ አመላክተዋል፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ወይዘሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው የመድረኩን አስፈላጊነት ሲያብራሩ፤ የምክር ቤቱ አባላት በወከሏቸው መራጮች ዘንድ የሚስተዋሉትን የሰላም እና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በዘላቂነት ዕልባት ለመስጠት ያግዛል ብለዋል፡፡

የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ክቡር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ፤ ሀገሪቱ በተግዳሮቶች ውስጥ ባለችበት በዚህ ወቅት፣ በሦስቱም ተቋማት ተጨባጭ ለውጦች እየታዩ መሆኑን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ የለውጡ መንግስት በመሠረተ-ልማት ዘርፍ ያለውን ኢ-ፍትሐዊ ተደራሽነት በዘላቂነት ለመቅረፍ በትኩረት እየሠራም እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ምክር ቤቱ እንደ አጠቃላይ፤ ተቋማቱ ተጨባጭ ለውጦችን እያስመዘገቡ እና የአሠራር ሥርዓታቸውን እያዘመኑ መምጣታቸውን አረጋግጧል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በሁሉም የመሠረተ-ልማት ዘርፎች ተጨባጭ ለውጦችን እያስመዘገበች እና በለውጥ ጎዳና እየተጓዘች እንደሆነም ምክር ቤቱ ተገንዝቧል፡፡

በ ተስፋሁን ዋልተንጉስ