(ዜና ፓርላማ)፤ ግንቦት 24፣ 2014 ዓ.ም.፤ ሱሉልታ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና አመራሮች፤ በውጤታማ ፓርላሜንታዊ ሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽን እንዲሁም ቀጣይነት ባለው የአመራር ክህሎት እንዲጎለብቱ አቅጣጫ ተመላከተ።

"አዲስ ፖለቲካዊ ዕይታ - አዲስ ሀገራዊ እመርታ" በሚል ርዕስ ለፓርላማ አባላት እና አመራሮች እየተሰጠ በሚገኘው ስልጠና ከቀረቡት የስልጠና ርዕሰ-ጉዳዮች፤ ፓርላሜንታዊ ሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽን ሥራዎችን የተመለከተው እና የአልተቋረጠ የአመራር ክህሎት መሻሻልን ማዕከል የአደረገው ተጠቃሽ ናቸው።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና አመራሮች፤ በሕገ-መንግስቱ የተሰጣቸውን ተግባር እና ኃላፊነት በሚፈለገው ደረጃ እና የጊዜ ገደብ በውጤታማነት ሊወጡ የሚችሉት፣ ተፈላጊው የተግባቦት (Communication) ዕውቀት እና ክህሎት ሲኖራቸው እንደሆነ፤ ስልጠናውን የሰጡት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ፣ ክቡር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) አስረድተዋል።

ምክር ቤታዊ ሥራዎች የሚፈለገውን ውጤት የሚያስመዘግቡት፤ የሕዝብ ተወካዮች ሀገራዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ የመረጣቸውን ሕብረተሰብ በጎለበተ የሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽን ክህሎት ሲያስረዱ፣ ሲያስጨብጡ እና ችግሮችን ሲፈቱ እንደሆነም፤ አስተባባሪው አስገንዝበዋል።

ስልጠናውን የተከታተሉት የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና አመራሮች፤ በስልጠናው ይዘት እና ወቅታዊነት መደሰታቸውን ገልጸዋል። ሕግ የማውጣት፣ የክትትል እና ቁጥጥር ሥራዎቻቸውን ለማከናወን፤ እንደዚሁም ሌሎች ተግባሮቻቸውን ለማከናወን፣ በዕውቀት እና በክህሎት የተደገፈ ውስጠ-ፓርላማ እንዲሁም አጠቃላይ ተልዕኮ-ተኮር የሚዲያ እና የተግባቦት ዓቅም እንደሚያሻቸው ተናግረዋል።

በሀገራችን የሚገኙ መገናኛ ብዙኃናትም ሕግ እና ሥርዓት ተከትለው ቢሠሩ፤ ጠንካራ ሀገረ-መንግስት ለመመሥረት ለሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት የበኩላቸውን ሚና እንደሚጫወቱ የጠቆሙት ሰልጣኞች፣ ትውልዱ በ 'በሬ ወለደ' ዓይነት የሐሰት ትርክት ሳይደናገር፤ መረጃዎችን በማስረጃዎች እያስደገፈ ለሀገሩ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም፤ ሰልጣኞቹ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

አሁን ባለንበት ሁኔታም፤ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የመገናኛ ብዙኃናት ማሻሻያ ወይም ጥገናዊ ለውጥ ሳይሆን የሚያስፈልጋት፣ የዘርፉን ሥር-ነቀል ለውጥ ማካሄድ ይኖርባታል ብለዋል። በየትኛውም ዘርፍ ያለው የሚድያ ሙያ እና ሥራ፤ ሀገር እና ትውልድ በመገንባት ላይ ማተኮር እንዳለበትም አመላክተዋል።

"የላቀ የስሜት ርጋታ እና ቀጣይነት ያለው የአመራር ስነ-ልቦና" በሚል ርዕስ ደግሞ ስልጠና የሰጡት፤ በመንግስት ተጠሪ ሚኒስቴር የስልጠና እና ዓቅም ግንባታ ዘርፍ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ፣ የተከበሩ ረዳት ፕሮፌሰር ምሕረቱ ሻንቆ ናቸው።

ሚኒስትር ዴኤታው በሰጡት ስልጠናም፤ የሕዝብ ተወካዮች ካለባቸው ሀገራዊ ኃላፊነት የተነሳ በጊዜያዊ ስሜት፣ ከየአካባቢው በሚነዙ ውዥንብሮች ሳይወናበዱ፤ የተጣለባቸውን ከፍተኛ ኃላፊነት በሰከነ አዕምሮ መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የምክር ቤት አባላት የሁልጊዜ ግብ መሆን የአለበትም፤ የዓለማችን ታላላቅ እና በሳል መሪዎች በተጓዙበት ዓይነት መንገድ በመሄድ፤ የአልተቋረጠ ግለሰባዊ፣ ተቋማዊ እና ሀገራዊ ለውጥ ለማስመዝገብ መጣር መሆኑን አመላክተዋል።

ሰልጣኞችም የስልጠናውን ርዕሰ-ጉዳይ እና ይዘት በጥሩ አስተያየት ተቀብለዋል። በቀጣይም ብዙ እንደሚጠበቅባቸው መገንዘባቸውን እና የሀገርን እና የሕዝብን አደራ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በ አሥራት አዲሱ