ዜና ፓርላማ:- የካቲት 30/2013 . (አዲስ አበባየሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ የገባበት መንገድ የሱዳን ህዝብ ፍላጎት ሳይሆን የሌላ አካል አጀንዳ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ አስታወቁ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ሱዳንና ኢትዮጵያ በወዳጅነታቸው የሚታወቁ ሀገራት ናቸው፤ አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ እና የሱዳን ህዝቦች ወዳጅ መሆናቸው ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም።

የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ መግባቱ ከሱዳናውያን ፍላጎት የመነጨ ሳይሆን የሌላ አካል አጀንዳ ይዞ ከመንቀሳቀስ የመነጨ ስህተት እንደሆነ ገልጸዋል።

 ኢትዮጵያ የህግ ማስከበር እርምጃ ላይ በነበረችበት ወቅት የሱዳን መንግስት ድንበር ጥሶ መግባቱ በእርግጠኛነት ትክክል እንዳልሆነ መናገር ይቻላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በሰከነ መንገድ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ፍላጎት እንዳላት ያመለከቱት አፈ ጉባኤው  ሱዳናውያን ይህን እድል ሊጠቀሙበት እንደሚገባ መክረዋል።

ሱዳናውያን በጥሞና ረጋ ብለው የተፈጠረውን ችግር ማጤን አለባቸው፤ አላግባብ የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው መግባታቸው ጥፋት ቢሆንም ቀድሞ ወደ ነበሩበት ቦታ ተመልሰው ወደ ድርድር መግባት እንደሚችሉ አመልክተዋል።