‹‹የበለፀገች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን እናስረክባለን››የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
‹‹የበለፀገች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን እናስረክባለን››የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
(ዜና ፓርላማ) ሰኔ 26 ቀን፣ 2017፤ አዲስ አበባ፤ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለልጆቻችንና ለመጭው ትውልዱ ለማስረከብ በሁሉም ዘርፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር ገለፁ፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት፤ ምክር ቤቱ ባካሄደው በ42ኛ መደበኛ ስብሰባው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡
የለውጡ መንግስት ለትምህርት ዘርፉ በሰጠው ትኩረት 29 ሺህ ልዩ ፍላጎት ለሚሹ ተማሪዎች እና ለ4.2 ሚለዮን ህፃናት ቅድመ መደበኛ ትምህርት እንዲከታተሉ መደረጉን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ የትምህርት ዘርፉን ከታች በመደገፍ እና ለውጤት ማብቃት ለትውልድ ግንባታው መሰረት የሚጥል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር አስረድተዋል፡፡
ሙህራንን ለማብቃት ባለፈው ዓመት 86 ሺህ ለሚሆኑ መምህራን ስልጠና እንደተሰጠ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸው፤ በቀጣይ የክረምት ወራት ለ82 ሺህ በላይ ለሚሆኑ መምህራን የአቅም ግንባታ ሙያዊ ስልጠና እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡
46 ሺህ መፅህፍት ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ማሰራጨት እንደተቻለና ጥምርታው (ratio) አንድ አጋዥ መፅሀፍ ለአንድ ተማሪ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
በትምህርት ዘርፉ ትልቅ ውጤት እየተመዘገበበት ያለ ዘርፍ በመሆኑ ሞደል እና አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ትምህርት ሚኒስቴር እየገነባ መሆኑን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡
የጤና ባለሙያዎች የደመወዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጋር በተያያዘ ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄው መሰረታዊ እና ተቀባይነት ያለው በመሆኑ አቅም በፈቀደ መልኩ ምላሽ የሚሰጥ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል ለዜጎች ተገቢውን ሙያዊ አገልግሎት በመስጠት የጤና መድህን ተጠቃሚነት ስርዓትን ማጠናከር እንደሚገባ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡
Copyright 2020 - All rights reserved. House of Peoples' Representatives