(ዜና ፓርላማ)፤ ግንቦት 19፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ አቶ ታገሠ ጫፎ፤ “ሀገራዊ ለውጡ አንጸባራቂ ድሎችን አስመዝግቧል” ሲሉ ሀገራዊ የለውጥ ጉዞውን አወደሱ።

አፈ-ጉባዔው ይህንን ያሉት፤ በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና ለሕዝብ ተወካዮች እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ከፍተኛ አመራሮች የብልጽግና ፓርቲ አባላት እየተሰጠ የሚገኘውን የዓቅም ግንባታ ስልጠና መርኃ-ግብር፣ በይፋ በከፈቱበት ወቅት ነው።

ስልጠናው “አዲስ የፖለቲካ ዕይታ፤ ለሀገራዊ እመርታ” በሚል መሪ ቃል ዙሪያ የሚያጠነጥን ሲሆን፤ ፖለቲካዊ መነቃቃትን ታላሚ አድርጎ ተጀምሯል - ከዝግጅቱ ሂደት እንደተረዳነው።

ስልጠናው እንደ ፓርቲ የጋራ ዓቋም፣ ተቀራራቢ አስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት እንድንይዝ ያደርገናል ያሉት የተከበሩ አፈ-ጉባዔ ታገሠ ጫፎ፤ ለውጡን በዘላቂነት በማረጋገጥ፣ የኢትዮጵያን ብልጽግና ዕውን ለማድረግ፤ ጠቀሜታው የላቀ ነው ብለዋል።

በሀገራዊ ለውጡ የመጀመሪያ ምዕራፍ እና በለውጡ ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን እና የተመዘገቡ ስኬቶችን አስመልክቶ፤ አፈ-ጉባኤው ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በሀገራዊ ለውጡ ከታዩት ዐበይት ጉዳዮች መካከል፤ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ሪፎርሞች የሚጠቀሱ አንደሆነ አፈ-ጉባዔው ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር፤ ለሥራ እና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማነቆ የሆኑ ሕጎች መሻሻላቸውንም አስታውሰዋል።

ሀገር-በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ለማምጣት ሁለንተናዊ ጥረት ስለመደረጉም የተናገሩት አፈ-ጉባዔው፤ በለውጡ ሂደት ስኬቶች፣ ፈተናዎች እና ብዙም ተስፋዎች እንዳሉ አክለው አስረድተዋል።

“ለውጡ፤ ለዘመናት የተሠራውን ሕዝብን የመለያየት እና እርስ በርስ እንዳይተማመን የተደረገበትን ሴራ በጣጥሷል፡፡የውጭ እና የውስጥ ችግሮችን ተቋቁሞ ሀገር እና ሕዝብን ለማሻገር እንዲሁም ተቀራራቢ አመለካከት እንዲያዝ አግዟል” አፈ-ጉባኤው እንዳብራሩት።

የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትሩ የተከበሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው የስልጠናውን አስፈላጊነት በገለጹበት ወቅት፤ በምርጫው ወቅት ለሕዝቡ ቃል የገባነውን ለመፈጸም ያግዘናል ብለዋል፡፡

ሀገሪቱ በውስጥም በውጭም እየተናጠች ባለችበት በዚህ ወቅት፤ የፓርላማውን ሥራዎች በብቃት ለመምራት እና በብልጽግና ፓርቲ መጀመሪያ ጉባዔ የተላለፉ ውሳኔዎችን እና የተቀመጡ አቅጣጫዎችን በተግባር አውርዶ ለመፈጸም ዓቅም የሚፈጥር ስልጠና እንደሚሆንም ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ የስልጠናውን ጠቃሚነት በተጨማሪነት ሲያስገነዝቡ፤ ሕዝቡ የሚያነሳቸውን የሰላም እና ደኅንነት፣ የመንግስታዊ አገልግሎት፣ የኑሮ ውድነት፣ የልማት ፕሮጄክቶች መጓተት እና ተያያዥ ችግሮችን በእውቀትና በክህሎት ለመፍታት የሚያስችል እንደሆነ አስገንዝበዋል።

ስልጠናው ገዢው ፓርቲ ውስጡን የሚያጠራበት እና መንግስት በሁለንተናዊ መልኩ ጎልብቶ እንዲቀጥል ፋይዳው የጎላ እንደሆነ የገለጹት የተከበሩ አቶ ተስፋዬ፤ ፓርቲውን በማጥራት መንግስትን ለማጠናከር የሚያስችል ነውም ብለዋል።

በ ተስፋሁን ዋልተንጉስ