(ዜና ፓርላማ)፤ ሰኔ 8፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሲሰጡ፤ “ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ለሚደረገው ድጋፍ መንግስት ዝግጁ ነው” በማለት፣ የመንግስትን አቋም አስገነዘቡ፡፡

መንግስት ጠንካራ ሀገር ለመሥራት በር ይከፍታል ብሎ ባመነበት በዚህ አካታች ምክክር፤ እንደ አንድ ባለድርሻ ንቁ ተሳታፊ ለመሆን እና ለኮሚሽኑ ሙሉ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዛሬው የምክር ቤቱ ጉባዔ አመልክተዋል፡፡

ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ተሳትፈውበት ምክክሩ ዳር ቢደርስ፤ ጠንካራ ሀገር ለመሥራት በር እንደሚከፍት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች እንዲሳተፉ በሩ ክፍት መሆኑን ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ አንዳንድ ፖለቲከኞች ‘በምክክሩ አንሳተፍም’ የሚል ሐሳባቸውን ትተው ገንቢ ሚና እንዲጫወቱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አካታች ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽኑን የማቋቋም፣ የመወያያ አጀንዳ የመቅረጽ እና ተሳታፊዎችን የመወሰን ሚና የሥራ አስፈጻሚው አካል ቢሆንም፤ መንግስት ግን ለምክክሩ ስኬታማነት ሲባል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለኮሚሽኑ መተውን ለምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ አስታውቀዋል፡፡

በነበረው ሂደት ጠንካራ ኮሚሽን በማቋቋሙ እና ሁነኛ ኮሚሽነሮችን በማስመረጡ፤ ምክር ቤቱን አመስግነዋል፡፡

ኮሚሽኑ በሚመራው ውይይት ሙሉ ለሙሉ መግባባት ላይ ባይደረስ እንኳን፤ ቀሪ ጉዳይ ካለ በሕዝብ ውሳኔ እንደሚሰጥም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመላክተዋል፡፡

በ አበባው ዮሴፍ