(ዜና ፓርላማ)፤ ሰኔ 27፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ታገሠ ጫፎ፤ “ዘላቂ ሀገራዊ ልማት ለማረጋገጥ አረንጓዴ አሻራ ማሳረፍ ትልቅ ጠቀሜታ እና ድርሻ አለው” በማለት፣ ስለአረንጓዴ አሻራ ተናገሩ፡፡

የተከበሩ አፈ-ጉባዔ ይህንን ያሉት፤ ከምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በዛሬው ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ችግኝ በተከሉበት እና የተከላ ሂደቱን በመሩበት ወቅት ባሰሙት ንግግር ነው፡፡

በዚህን ጊዜም የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብሩ በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ የመጣውን አጠቃላይ የደን ሽፋን ለማስተካከል እንዲሁም ዘላቂነት ያለውን ሀገራዊ ልማት ለማረጋገጥ ከፍተኛ አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንዳለው አቶ ታገሠ አስረድተዋል፡፡

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን የተተከሉት ችግኞች ስለመጽደቃቸው መከታተል እና መንከባከብ እንደሚገባውም አፈ-ጉባዔው አሳስበው፤ ሕዝቡ ችግኝ ሲተክል ለምግብነት የሚውሉ ሀገር-በቀል ዛፎችን መትከል እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

ወቅቱን የጠበቀ ዝናብ እንዲኖር እና የሕዳሴ ግድባችንን ሂደት ዕውን ለማድረግ የአረንጓዴ አሻራ የማይተካ ሚና እንዳለው የገለጹት ደግሞ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ሎሚ በዶ ናቸው፡፡

ምክትል አፈ-ጉባዔዋ የአረንጓዴ አሻራ ሥራ የታለመለትን ግብ እንዲመታ እና ሀገራችን በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም-ዓቀፍ ደረጃ ተምሳሌት እንድትሆን፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የችግኝ ተከላ መርኃ-ግብሩን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

ዓለም-አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና እየተመናመነ የመጣውን የደን ሽፋን ወደ ነበረበት ለመመለስ፤ በዘንድሮው ዓመት 7 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የተከበሩ አቶ አሰማኸኝ አስረስ ናቸው፡፡

የችግኝ ተከላ መርኃ-ግብር ዋናው ግብ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን የተተከሉት ችግኞች ስለመጽደቃቸውም መከታተል እንደሆነ አቶ አሰማኸኝ ጠቅሰው፤ ባለፉት ዓመታት በተተከሉት ችግኞች እና በተጠናው ጥናት መሠረት ከ80 እስከ 84 በመቶ መጽደቅ እንደቻሉ አውስተዋል፡፡

ሁሉም ዜጋ ችግኝ ሲተክል ለእያንዳንዱ ችግኝ ወጪ እንደወጣበት እያሰበ ተክሎ መንከባከብ እንዳለበትም፤ አቶ አሰማኸኝ ተናግረዋል፡፡

የምጣኔ-ሀብታችን ምንጭ ግብርና በመሆኑ እና የወደፊት ኢትዮጵያን ዕጣ-ፋንታ ለመወሰን የአረንጓዴ አሻራ ሥራው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የመርኃ-ግበሩ ተሳታፊ መሆን እንዳለበት የገለጹት ሌላኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የተከበሩ አቶ አሽኔ አስቲን ናቸው፡፡

የተከበሩ አቶ አሽኔ አክለውም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዓለም-አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ተረድቶ፤ ችግሩን ለመቋቋም እና የምግብ ዋስትናችን ለማረጋገጥ፣ ለምግብነት የሚሆኑ ችግኞችን መትከል አለበት ብለዋል፡፡

በ ስሜነው ሲፋረድ