"ሕገ- መንግሥታዊነት በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ ዕሳቤዎችን መፈፀም ነው"

---- የተከበሩ ተስፋዬ በልጅጌ (/) ----

(ዜና ፓርላማ) መጋቢት 26 2017 .ም፤ ሦስተኛው የፓርላማ ዜጎች ፎረም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።

"ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊነት በኢትዮጵያ" በሚል የመወያያ ርዕስ ሕገ መንግሥታዊ ታሪክ ቅቡልነትና ተግዳሮት እንዲሁም ተግባራዊነት ላይ ያተኮሩ ፅሑፎች ቀርበዋል።

"ሕገ- መንግሥታዊነት በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጡ መሠረታዊ ዕሳቤዎችን ማክበር መሆኑን የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር የተከበሩ ተስፋዬ በልጅጌ (/) ገልጸዋል።

አያይዘውም በሕግና በሥርዓት የሚመሩ ጠንካራና ብቁ ተቋማት መኖር የሕገ መንግሥታዊነት መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።

ህዝባችን በሕገ-መንግሥቱ ላይ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ሁሉንም አካላት ባሳተፈ ውይይት  መስተካከል ይችላሉም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከዜሮ የምትጀምር አገር መሆን የለባትም ያሉ ሲሆን ከትላንት የመጡ ጉዳዮችን በማረምና በማስተካከል ከዘመኑ ጋር እያጣጣሙ መጠቀም እንደሚገባ አመላክተዋል።

ከዜሮ መጀመራችን የተረጋጋ ሀገረ መንግሥት እንዳይኖር የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ወደኃላ እንዲቀርና ጠናካራና ብቁ ተቋማት እንዳይፈጠሩ አድርጓል ብለዋል።

ሕገ መንግሥቱ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ቅቡልነት እንዲያገኝ ሁሉም አካላት የተፈጠረውን የመነጋገርና የመወያየት ዕድል በመጠቀም የራሳቸውን አሻራ እንዲያሳርፉ ጥሪ አቅርበዋል።