(ዜና ፓርላማ)፤ ሰኔ 20፣ 2014 ዓ.ም.፣ አዲስ አበባ፤ “አዋጆች ሲወጡ ለረጅም ጊዜ የሚያገለግሉ፣ ጥራት ያላቸው እንዲሁም ከሕገ-መንግስቱ የማይጣረሱ መሆን ይገባቸዋል” ሲል በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስገነዘበ።

ቋሚ ኮሚቴው ይህንን ያለው፤ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም በወጡት አዋጆች ዙሪያ ለመወያየት፣ በዛሬው ዕለት በጠራው የአስረጂ መድረክ በሰጠው አስተያየት ነው።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ዕጸገነት መንግስቱ እንደገለጹት፤ በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ አዋጆች ዘመን ተሻጋሪ፣ የዜጎችን መብት እና ጥቅም የሚጠብቁ እንዲሁም እያደገ የሚሄደውን የቴክኖሎጂ ዕድገት ያገናዘቡ መሆን ይገባቸዋል።

ቋሚ ኮሚቴው በቀጣይ፤ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም በወጡት አዋጆች ላይ፤ ከተቋማቱ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፋ ያለ ውይይት እንደሚያደርግ የተከበሩ ዕጸገነት መንግስቱ ገልጸዋል።

በውይይቱ ላይ የተቋማቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን፤ በሠራተኞች የደመወዝ እና የጥቅማ-ጥቅም ክፍያ አወሳሰን፣ የተቋማቱን የሥራ አስፈጻሚ አካላት የሹመት ጉዳይ፣ ተቋማቱን በቴክኖሎጂ የማዘመን ሂደት እንዲሁም ዜጎች መረጃን በፍጥነት የማግኘት መብትን የሚያስጠብቁ አዋጆች እንደሆኑም ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል።

በ ሚፍታህ ኪያር