(ዜና ፓርላማ)፣ ጥር 26፣ 2015 ዓ.ም፤ በምክር ቤቱ የሚወጡ ሕጎች ዜጎች ከደረሱበት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን ጋር ተጣጥመው ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ እና ችግር ፈቺ መሆን ይገባቸዋል ሲሉ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ገለጹ።

ምክትል አፈ-ጉባዔዋ ይህንን የገለፁት በአዳማ ከተማ ለኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት በግብርና ምርት ውል (contract farming) እና በዕፅዋት ዘር ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ለግንዛቤ ማስጨበጫ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ነው።

በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን በዘርፉ የተሰማሩ የአርሶና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚነት ከፍ ማድረግ ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊሰራ ይገባል ያሉት ምክትል አፈ-ጉባዔዋ፤ ለዚህም መሰረት የሚሆኑ ሕጎችና ደንቦች ሲወጡ ጥራታቸውን የጠበቁ እና የዜጎችን ሁለንተናዊ ፍላጎት ከግምት ያስገቡ መሆን ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

ምክትል አፈ-ጉባዔዋ አያይዘውም፤ ለአርሶና አርብቶ አደሮች ከግብዓት አቅርቦት በተጨማሪ ላመረቱት ምርት የገበያ ትስስር በመፍጠር የተጠቃሚነት ደረጃቸውን ከፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር የተከበሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው መንግስት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና ለውጥ ለማምጣት የሚያግዙ አዳዲስ አሰራሮችንና ደንቦችን በመዘርጋት ከአምስት መቶ በላይ ከውጭ ሀገር በሚገቡ የግብርና ስራ ማሳለጫ መሳሪያዎች እና የግብርና ምርት ግብዓቶች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ መፈቀዱን አስታውሰው፤ ይህም የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አረጋግጠዋል፡፡

የግብርና ምርትና ምርታማነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ከተፈለገ አምራቾች በሚያመርቱት ምርት ላይ እሴት እንዲጨምሩና ተገቢውን ክፍያ እንዲያገኙ ማስቻል ይገባል ያሉ ሲሆን፤ ለዚህም የግብርና ምርት ውል (contract farming) እና የዕፅዋት ዘር ረቂቅ አዋጅ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ጠቁመዋል።

የግብርና ምርቶች ውል እና የዕፅዋት ዘር ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ የመነሻ ፅሑፍ በዘርፉ ባለሙያዎች የቀረበ ሲሆን፤ በቀረበው ረቂቅ ላይ ከተሣታፊዎች አስተያየትና ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

የግብርና ዘርፉን ለማሳደግ እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራት ለመጨመር ያስችላሉ በተባሉት የግብርና ምርቶች ውል እና የዕፅዋት ዘር ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ በግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በተከበሩ አቶ ሰለሞን ላሌ ውይይት እየተደረገበት ነው፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament

በዩቲዩብ https://www.youtube.com/@FDREHOPR

በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews

በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr

በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ