(ዜና ፓርላማ)፤ ግንቦት 29፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ "የግብርና ሚኒስቴር የምግብ ፍላጎትን እና አቅርቦትን ለማመጣጠን በትኩረት መሥራት ይጠበቅበታል" ሲል መልዕክት አስተላለፈ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው መልዕክቱን ያስተላለፈው፤ የግብርና ሚኒስቴርን የ2014 በጀት ዓመት የ9 ወር የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አስመልክቶ ዛሬ ባካሄደው 5ኛ ልዩ ስብሰባ ማጠቃለያ በሰጠው ግብረ-መልስ ነው፡፡

ግብረ-መልሱን ያቀረቡት የኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ሰለሞን ላሌ፤ ኮሚቴው የሚኒስቴሩን እና የተጠሪ ተቋማቱን ሪፖርት የመረመረ እና እያከናወኗቸው ያሉትን ተግባራት በመስክ ምልከታ ጭምር ያረጋገጠ እንዲሁም ግብረ-መልስ የሰጠ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ሰብሳቢው፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እና ተጠሪ ተቋማት ተናብበው መሥራት መቻላቸውን፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የውጪ ምንዛሬን ለማዳን በግብርናው ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትን ኮሚቴው በጠንካራ አፈጻፀም መመልከቱን ተናግረዋል፡፡ አክለውም በማዳበሪያ ግዥ እና አቅርቦት፣ በመኸር የማሳ ሽፋን እና በአረንጓዴ አሻራ ዙሪያ የተሠሩ ሥራዎችም የሚደነቁ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መዋቅራዊ ሽግግር ማምጣቱ፣ ከዚህ በፊት ከነበረበት የነቀፋ የኦዲት ግኝት መውጣቱ፣ አመራሩ ለሪፎርም ሥራ ትኩረት መስጠቱ እና በዘርፉ ለዜጎች የስራ ዕድል ፈጠራ እገዛ ማድረጉንም የተከበሩ አቶ ሰለሞን ላሌ በአዎንታዊ አፈጻጸም ጠቃቅሰዋል፡፡

በሌላ በኩል ሚኒስቴሩ በርካታ ውጤታማ ሥራዎችን ቢያከናውንም፤ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ አሁንም የዜጎች የምግብ ፍላጎት እና አቅርቦት አለመመጣጠኑን፣ ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶች አነስተኛ መሆናቸውን፣ የግብርና ሥራው ግለቱን ጠብቆ አለመከናወኑን በክፍተት አንስተዋል፡፡

አያይዘውም፤ በቀጣይ የለውጥ ሥራን ታች ድረስ የማውረድ፣ የማዳበሪያ አቅርቦት እና የኮምፖስት ሥራ፣ የከተማ ግብርናን፣ የግብርና ሜካናይዜሽን ሥራን የማስፋፋት፣ የውኃ አማራጮችን የመመልከት እንዲሁም በዘርፉ ለዜጎች የሥራ ዕድልን የመፍጠር ተግባራት በትኩረት ሊሠራባቸው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በ ኃ/ሚካኤል አረጋኸኝ