በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ “በኢንዱስትሪ እና ማዕድን ዘርፍ የተሰማሩ የሙያ እና የንግድ ማኅበራት፣ እያጋጠሟቸው ያሉትን ችግሮች ለመፍታት፣ የመፍትሔው አካል መሆን አለባቸው” ሲል አቅጣጫ ሰጠ፡፡

ይህ አቅጣጫ የተሰጠው፣ የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢንዱስትሪ እና ማዕድን ዘርፍ ከተሰማሩ የሙያ እና የንግድ ማኅበራት ጋር በዛሬው ዕለት በማኅበራቱ ችግሮች ዙሪያ የመጀመሪያ ዙር ውይይት ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡

በውይይቱ ወቅት፤ የፀጥታ ችግር፣ ተቋማት ከዕቅድ ጀምሮ በሚደረጉ ውይይቶች ማኅበራቱን አለማሳተፍ፣ የፖሊሲ ክፍተቶች፣ የግብዓት እና የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት፣ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ትኩረት አለመስጠት፣ የባንክ ብድር ወለድ መጨመር፣ በተቋማት ያሉ የአሠራር ችግሮች እና ያለመናበብ ክፍተቶች እና የመሳሰሉት፤ በማኅበራቱ በኩል ተጠቅሰዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አማረች ባካሎ (ዶ/ር)፤ ኢንዱስትሪ ለአንድ ሀገር ምጣኔ-ሀብት የጀርባ አጥንት እንደሆነ ጠቅሰው፣ በማኅበራቱ የተነሱትን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት፤ ማኅበራቱ ራሳቸው መፍትሔ አመንቺ እና የመፍትሔው አካል መሆን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

በማኅበራቱ በኩል የተነሱትን ችግሮች ተባብሮ ለመፍታትም፤ ቋሚ ኮሚቴው ከሚመለከታቸው አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ጋር ውይይት እንደሚያደርግ፣ ሰብሳቢዋ አስታውቀዋል፡