"በበጀት ዓመቱ በዘጠኝ ወራት 6 መቶ 53 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰብስቧል"
"በበጀት ዓመቱ በዘጠኝ ወራት 6 መቶ 53 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰብስቧል"
--- ክብርት ወ/ሮ አይናለም ንጉሤ ----
(ዜና ፓርላማ) ሚያዚያ 28 ፣ 2017 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ የገቢዎች ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ በዘጠኝ ወራት ውስጥ 6 መቶ 53.2 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ክብርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ ገልጸዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 28ኛ መደበኛ ስብሰባ የገቢዎች ሚኒስቴርን የ2017 በጀት አመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ያደመጠ ሲሆን፤ የምክር ቤት አባላት በርካታ ጥያቄዎች አቅርበው ክብርት ሚኒስትሯ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት አይናለም ንጉሴ አያይዘውም፤ ተቋሙ ገቢን ለማሳደግ በሰራው ሥራ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከእቅድ በላይ ማሳካት መቻሉን አስረድተዋል፡፡
ተሰብሳቢ ገቢ ከባለፉው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 2 መቶ 79 ቢሊዮን ብር ብልጫ መኖሩን ክብርት ሚኒስትሯ አስረድተዋል፡፡
ተቋሙን በቴክኖሎጂ በማዘመን እና የኤሌክትሮኒክ ክፍያን በማጠናከር ህገ ወጥ አሰራሮችን ለመከላከል እምርታዊ ለውጦችን ማምጣት መቻሉን ክብርት ወ/ሮ አይናለም አስረድተዋል፡፡
ታማኝ ግብር ከፋዮችን ለማበረታታ የዕውቅና እና ሽልማት ፕሮግራም በማዘጋጀት ዘርፉን ለመደገፍ የንቅናቄ ስራ መሰራቱን ክብርት ሚኒስትሯ ጠቁመዋል፡፡
የሀገርን የፋይናንስ አቅም በማጎልበት የውስጥ ገቢን አቅም በማጠናከርና በማጎልበት የዜጎችን የመልማት ጥያቄ ለመመለስ ስለሚያግዝ ዘርፉን መደገፍ እንደሚገባ ክብርት ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ክቡር አቶ ደበሌ ቀበታ በበኩላቸው፤ የሀገር ዕድገት ማነቆ የሆነውን ኮንትሮባንድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሰነድ በማዘጋጀት በጥናት ላይ የተመሰረት ስራ በመስራት ከምንጩ ለማድረቅ ህገ ወጥ ነጋዴዎች የገበያ ህግና ስርአትን ተክተለው እንዲሰሩ ለማስቻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከጫት ንግድ ጋር እያጋጠመ ያለውን ችግር ለማፍታት የግብይት ማዕከል በማዘጋጀት ከዘርፉ አርብቶ አደሩ እና ሀገር ተጠቃሚ የምትሆንበትን አሰራር እየተመቻቸ መሆኑንም ክቡር ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡
የዘመነ የጉምሩክ የጠረፍ የንግድ ስርዓት በመዘርጋት የገቢና የወጪ ምርቶች እና እቃዎች ጋር በተያያዘ ኮንትሮባንድ ግብይትን ለማስቀረጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል፡፡
የፕላን፣በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ደሳለኝ ወዳጀ ተቋሙ የገቢ አቅምን በማጠናከር በተሰራው ስራ ለውጦች መኖራቸውን ጠቁመው፤ በቀጣይ ወራት የሚጠበቅበትን ገቢ ለመሰብሰብ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የግብር አሰባሰብን ዲጂታላይዝድ ማድረግ፤ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ማረጋገጥ፤ አዳዲስ ነጋዴዎችን ወደ ግብይት ስርአቱ ማስገባት እንዲሁም ዜጎች ለግብር ስርአቱ ተገዥ እና ታማኝ የግብር ከፋይ እንዲሆኑ የግንዛቤ ስራ መሰራት እንዳለበት የተከበሩ አቶ ደሳለኝ ወዳጀ አሳስበዋል፡፡
ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ እቃዎች ለታለመላቸው ዓለማ መዋላቸውን የሚመለከታቸው አካላት ማረጋገጥ እንዳለባቸው የምክር ቤት አባላት አስገንዝበዋል፡፡
ከኮንትሮባንድ፤ ከግብር ስወራ እና ከህገ ወጥ አሰራሮች ጋር በተያያዘ የሀገርን ዕድገት ስለሚጎዱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ በጥናት ላይ ተመስርቶ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት እንደሚጠበቅበት የምክር ቤት አባላት አሳስበዋል፡፡
(በመኩሪያ ፈንታ )
Copyright 2020 - All rights reserved. House of Peoples' Representatives